Ethio Newsflash

Ethio Newsflash

Share

22/08/2022

“የዘንድሮው ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ተሰርቆ ወጥቷል” ከሚል ፅሁፍ ጋር በስፋት የተጋራው ምስል በቅንብር የቀረበ ነው።

(በኢትዮጵያ ቼክ የቀረበ)

ከ865 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉትና "Mereja TV" የሚል ስያሜ ያለው የፌስቡክ ገጽ “የዘንድሮው ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ተሰርቆ ወጥቷል” የሚል መረጃ ማጋራቱን ተመልክተናል።

ከመረጃው ጋር የፈተና ቡክሌት አብሮ የተያያዘ ሲሆን የፌስቡክ ገጹ መረጃውን ያገኘው ከመ/ር ዘመድኩን በቀለ መሆኑን ጠቅሷል። መረጃውን ከ3,700 በላይ ሰዎች ላይክ ያደረጉት ሲሆን 838 ጊዜ ሼር ተደርጓል። በተመሳሳይ ሌሎች የፌስቡክ ገጾችና የቴሌግራም ቻናሎች ይህንኑ መረጃ በስፋት ማጋራታቸውን አስተውለናል።

ኢትዮጵያ ቼክ የመረጃውን ትክክለኛነት ለማጣራት የተጋራውን ቡክሌት የመረመረ ሲሆን መረጃው ሀሠተኛ መሆኑን አረጋግጧል፣ ለዚህም የተጋራውን ቡክሌት በንጽጽር መርምሯል። በተጨማሪም የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎትን አነጋግሯል።

በንጽጽሩም “የዘንድሮ” ነው ተብሎ የተጋራውን የታሪክ ፈተና ቡክሌት በ2013/14 ዓ.ም የተሰጠ እንጂ አዲስ አለመሆኑን ተመልክተናል። በቡክሌቱ ላይ የሚታዩት ጥያቄዎችም ከ2013/14 ዓመተ ምህረቱ ፈተና ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ መሆናቸውን አይተናል።

ሀሠተኛውን መረጃ ያሰራጩት አካላት በፈተናው ቡክሌት ግርጌ ላይ የሚገኘውን ዓመተ ምህረት ኤዲት በማድረግ ከ2013/14 (2021) ወደ 2014/15 (2022) የቀየሩት ሲሆን በዓመተ ምህረቶቹ መሃል መቀመጥ የነበረበት የእዝባር ምልክት (/) ካለመጠቀም ጀምሮ ግልጽ የመነካካት ስራ መስራታቸው ይታያል።

ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳሬክተር ዶ/ር እሸቱ ከበደ የተሰራጨውን መረጃ መመልከታቸውን ገልጸው ሀሠተኛ መሆኑንና የተጋራው የፈተና ቡክሌት በ2013/14 (2021) ዓ.ም የተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

በ2013/14 (2021) ዓ.ም የተሰጠን የታሪክ ፈተና ለንጽጽር ይረዳ ዘንድም ለኢትዮጵያ ቼክ አሳይተዋል። ዋና ዳሬክተሩ በ2013/14 (2021) ዓ.ም የተሰጠ የኬሚስትሪ ፈተናም በተመሳሳይ ሁኔታ ዓመቱ ኤዲት ተደርጎ ሲሰራጭ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ዶ/ር እሸቱ ተፈታኝ ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መሰል መረጃዎችን ከማመናቸው በፊት የአሰራጩን ታማኝነት እንዲያጣሩና ትክክለኛነቱን እንዲመረምሩ መክረዋል።

ፈተናን የተመለከተ መረጃ ሲፈልጉም የፌስቡክ ማረጋገጫ ሰማያዊ ምልክት ባለው የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የፌስቡክ ገጽ በግልም ሆነ በቡድን መልዕክት እንዲልኩ አበረታተዋል።

የአገር አቀፍ ፈተናን የተመለከቱ ሀሠተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላትም “ፖለቲካን ከታዳጊዎች ህይዎት ቢለዩ መልካም ነው” ሲሉ አሳስበዋል።

25/05/2022

#ኒውስፍላሽ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያንዳንዳቸው ከ350 ሚልዮን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው አምስት የጭነት አውሮፕላኖችን ከቦይንግ ኩባንያ አዘዘ።

ኢትዮ ኒውስፍላሽ ዛሬ የደረሰው መረጃ እንደሚጠቁመው አየር መንገዱ ያዘዘው 777 የተባለውን እጅግ ዘመናዊ የጭነት አውሮፕላን ነው። አውሮፕላኑ በአለም ላይ ካሉ የጭነት (cargo) አውሮፕላኖች ትልቁ እና ዘመናዊው ሲሆን ከሌሎች አውሮፕላኖች በ17% የቀነሰ የነዳጅ ፍጆታ ያለው ነው።

25/05/2022

#ኒውስፍላሽ የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ትናንት ድርጅቱን እንዲመሩ በድጋሜ ሲመረጡ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተቃውሞ አሰምተው ነበር!

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል አምባሳደር የሆኑት ማህሌት ሀይሉ በቪድዮው ላይ በሚታየው መልኩ የአፍሪካ ቡድን ለዶ/ር ቴድሮስ በቦትስዋና አማካኝነት እንዳይቀርብ ጠይቀው ነበር። በመጨረሻ ግን ምርጫው ተካሂዶ ዶ/ር ቴድሮስ ድርጅቱን በቀጣይ አመታት እንዲመሩ ተመርጠዋል።

24/05/2022

#ኒውስፍላሽ የጠ/ሚር ፅ/ቤት የታይም መፅሄትን በስም ማጥፋት ወንጀል ከሰሰ!

ትናንት ከአለም ተፅእኖ ፈጣሪዎች አንዱ ብሎ መፅሄቱ የመረጣቸው ጠ/ሚር አብይ ላይ "ሆን ተብሎ የስም ማጥፋት እና ስብእናን የማጉደፍ ስራ ተሰርቷል" ይላል በቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም ተፅፎ ከደቂቃዎች በፊት ለሚድያዎች የተሰራጨው ደብዳቤ።

ለዚህም አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ መፅሄቱ ተጠይቋል። በትናንትናው እለት የመንግስት ሚድያዎች ጉዳዩን እንደበጎ ነገር በሰበር ዜና ሲያራግቡት እንደነበር ይታወሳል።

Want your business to be the top-listed Media Company in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Address


4 Kilo
Addis Ababa