YMG

YMG

Share

29/05/2019

ለወንጀል ምርመራ ተብሎ ባልታሰበ አጋጣሚ የመያዝ አድሎች እና ከዘፈቀደ የሞባይል ስልክ መስመር እና ቀፎ አጠቃቀም መውጣት አስፈላጊ መሆኑን የሚያመለክቱ ወቅታዊ አንኳር ጉዳዮች

በ፦ ተመስገን ሽፈራዉ

1/ የቼክ፣ የሞባይል ባንኪንግ፣ የሞባይል ካርድ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች

አገልግሎት ለማቀላጠፍ በሚል አላማ እና ሞባይል ስልክ ከባለቤቱ እጅ አይወጣም በሚል ሀሳብ ባንኮች በሞባይል ገንዘብ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርጉ አሰራሮችን የዘረጉ ቢሆንም በተገላቢጦሽ ደግሞ ከባለ ሞባይሉ ግለሰብ እና ከቴሌ መ/ቤት የጥንቃቄ ጉድልት የተነሳ አሁን ላይ ደግሞ በባንክ ያለው ገንዘባችን በሂሳባችን ውስጥ ውሎ ለማደሩ እንድንሰጋ የሚያደርጉ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡

ቼክ ከመከፈሉ በፊት የቼኩ ባለቤት ፈቃድ መኖሩን ለማረጋገጥ ለባንኩ ባስመዘገበው ሞባይል ስልክ ደውሎ መጠየቅ በተሰረቀ ቼክ በተመሳሳይ ፊርማ የሚመዘበርን የሰዎች ገንዘብ ለመከላከል በሚል ባንኮች እንደ አሰራር ሲከተሉት ቆይተዋል፡፡ ይህ አሰራር በመኪና ላይ፣ ከቤት እና ከንግድ መደብር ውስጥ በሚፈጸም ዘረፋ ወቅት አብረው ሌቦቹ በሚያገኙት ቼክ ፊርማ አመሳስለው ገንዘብ ከባንክ እንዳያወጡ ሲከላከል እንደቆየ አስረጂ የሆኑ አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ላይ ደግሞ በተጠና ሁኔታ ቼክ ሰርቆ እና መሰረቁም እንዳይታወቅ በማድረግ በሌላ በኩል ሀሰተኛ መታወቂያ በማሰራት የባለቼኩን ስልክ በማዘጋት እና አዲስ መስመር በማውጣት በተመሳሳይ ፊርማ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በማዘዝ ባንኩም ለማረጋገጥ ስልክ ሲደውል አስቀድሞ ተዘግቶ እንደገና በተከፈተው መስመር እራሱ ሌባው ይከፈል ብሎ መልስ እየሰጠ የድርጅት እና የግለሰብ ገንዘብ ከባንክ ወጥቶ ከቀናት ወይም ወራት ቆይታ በኋላ ድርጅቱ ወይም ግለሰቡ ባንክ ሲሄድ ገንዘቡ ስለ መውጣቱ መርዶ የሚሰማበት አጋጣሚ እየተፈጠረ ነው፡፡

የነበረን መስመር ለማዘጋት እና አዲስ መስመር ለማውጣት ቴሌ የሚከተለው አሰራር አንደኛው መታወቂያ በማየት ሲሆን /ኮፒ አድርጎ እንኳን አያስቀምጥም/ ይህም በሀገሪቱ ሀሰተኛ መታወቂያ እንደ ልብ ተሰርቶ የሚቀርብበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያላስገባ ነው፡፡ ሁለተኛው መንገድ በተለይ ለማዘጋት በቅርብ የደወልክበትን ወይም የተደወለለልህን ሶስት ስልኮች ተናገር የሚል ሲሆን ይህም በጥናት ስርቆት ለሚፈጽም የቅርብ ሰው እና ተባባሪው ቀላል ስራ ነው፡፡

ብዙ ኢትዮጵያውያን ሞባይላቸው መስመሩ የተለየ ባህሪ ሲያመጣ ቴሌ ሄዶ ከመጠየቅ እና ለባንኮች ከማሳወቅ ተዘናግተው ሌላ መስመር እየተጠቀሙ የመቆየት ልምድ ያላቸው ሲሆን መስመር ከተዘጋ በኋላ እንደገና ሲከፈት መስመሩ ሌላ ቀፎ ውስጥ እስካልገባ ድረስ የነበሩ የባንክ አገልግሎቶች ባሉበት ስለሚቀጥሉ መስመሩን እንደ አዲስ ያወጣው አካል የሚፈልገውን ነገር የማድረግ እድል ይከፈትለታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሌላ ሰው ስም የወጣ ሞባይል መስመር መያዝ እና እሱንም ለባንክ ማስመዝገብ የተለመደ ስለሆነ በስሙ ያወጣው ሰው አዘግቶ እንደገና በማውጣት ወንጀሉን ለመፈጸም ምቹ ሁኔታ ይፈጠርለታል፡፡

2/ የተጣሉ የሞባይል መስመሮች አንስቶ ቀፎ ውስጥ ማስገባት፣ ከማያውቁት ሰው አገልግሎት ላይ የዋለ የሞባይል ቀፎ መግዛት ወይም የተጣሉ የሞባይል ቀፎዎች ውስጥ የራስን ሲም ማስገባት

በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቀላል ስርቆት ተብለው በየቀኑ ምርመራ መዝገብ ፖሊስ ከሚከፍትባቸው አቤቱታዎች አብዛኛው ሞባይል ስልክ መንጠቅ ሲሆን ከባድ ስርቆት፣ ዘረፋ፣ ውንብድና፣ ማታለል፣ ሰው መግደል . . . ወዘተ የመሳሰሉት ወንጀሎች ሲፈጸሙ ደግሞ አብሮ የተበዳይ ሞባይል ስልክ የሚወሰድበት ሁኔታ የተለመደ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም ሞባይል ስልክ ለመስረቅ ተብሎ ሰው ተገድሎ ወይም ከባድ አካል ጉዳት ደርሶበት ይገኛል፡፡ ሞባይል ስልክ ከተወሰደ በኋላ ወንጀለኛው ወዲያውኑ ሞባይል መስመሩን አውጥቶ ባገኘበት ቦታ ጥሎ ቀፎውን ይሸጣል ወይም ለሚቀርበው ሰው ይሰጣል፡፡ ሰዎች በአጋጣሚ ወድቆ ያገኙትን መስመር ቀፏቸው ውስጥ ለማስገባት ወደኋላ አይሉም፡፡ ፖሊስ ደግሞ ወንጀሉ ከባድ ሲሆን በፍ/ቤት ትእዛዝ የተበዳይን /የተሰራቂውን ወይም የሟቹን/ ሞባይል መስመር የት ቦታ እንዳለ በኔት ወርክ ሲከታተል ባለቀፎውን ይይዛል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ሞባይል ቀፎዎች የራሳቸው መለያ ኢኤምአይ ኮድ ያላቸው ሲሆን ወንጀል ፈጻሚዎች ቀፎዎቹን የሸጡለት ሰው ወይም ቀፎውን ጥለውት ከሆነ ያገኘው ሰው ወይም ወንጀለኛ መሆኑን የማያውቅ የወንጀለኛው ጓደኛ በአጋጣሚ ሞባይል ቀፎው ውስጥ የራሱን ሲም ሲያስገባ በፍ/ቤት ፈቃድ በኔት ወርክ ክትትል ፖሊስ ባለ ሲሙን ይይዛል፡፡

በሁለቱም አጋጣሚ የሚያዙ ሰዎች ንጹህ የመሆን እድላቸው አሁን አሁን ሰፊ ነው፡፡ በተግባርም አጋጥሟል፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ከባድ ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች ፖሊስ በዚህ ዘዴ ሊያገኛቸው እንደሚችል ስለሚያውቁ መስመሩንም ቀፎውንም ይጥላሉ ወይም ይሸጣሉ፡፡ ነገር ግን ፖሊስ አልፎ አልፎ ወንጀለኞችም ቀፎውን እና መስመሩን ሲጠቀሙ ይዞ ስለሚያውቅ ወይም ይዞ እየተጠቀመ ያለው ሰው ያገኘበትን ቦታ እና ጊዜ መሰረት አድርጎ ለምርመራው ፍንጭ የሚሆን መረጃ ሊያገኝ ስለሚችል /ለምሳሌ አዲስ አበባ ሰው ገድሎ ከአዲስ አበባ ርቆ ባለ ቦታ ሲሙን ጥሎት ከሆነ እና ያገኘው ሰውም ያገኘበትን ቦታ በትክክል ቢናገር የወንጀለኛው ዱካ መከታተያ መንገድ ሊሆን ስለሚችል/ የተበዳይ መስመር ወይም ቀፎ በእጁ የተገኘበት ሰው ከወንጀለኛው ጋር ግንኙነት አለው ወይስ የለውም የሚለውን እስከሚጣራ እና ተጨማሪ ፍንጭ እስሚገኝ ድረስ ታስሮ ለምርመራ መቆየት ይከሰታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሞባይል ቀፎው የተገኘበት ሰው ገዝቸው ነው የሚል ምክንያት ብዙ ጊዜ የሚያቀርብ ቢሆንም ከማን እንደገዛው ማስረዳት ስለማይችል እንዲሁም የገዛበት ዋጋ ከመደበኛው እጅግ ያነሰ ስለሚሆን መሰረቁን ማወቅ እየተገባው የተሰረቀ እቃ ገዝቷል በሚል በመሸሸግ ወንጀል የመከሰስ የመጨረሻ አማራጭ ጭምር ይጠብቀውና ለመከላከል ተቸግሮ ሊቀጣ ይችላል፣ ተከላክሎ ነጻ ቢወጣ እንኳን አላግባብ በራሱ ጥንቃቄ ጉድለት የሚደርስበት የጊዜ፣ የጉልበት፣ የገንዘብ ኪሳራ ቀላል አይሆንም፡፡

3/ የሞባይል መስመር የተከፈተ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንት መጠለፍ

በስፋት ሰው የሚጠቀመው ፌስቡክ አካውንት በስልክ መስመር የተከፈተ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢሜይልም በአሁን ጊዜ ሲከፈት ሞባይል ስልክ ይጠይቃል፡፡ ሞባይል ስልክ ደግሞ ከላይ በገለጽኩት መንገድ ከቴሌ በቀላሉ ተዘግቶ እንደገና የሚከፈትበት አጋጣሚ ታይቷል፡፡ ከዚህ አንጻር ሞባይል መስመሩ ተዘግቶ እንደገና በሌላ ሰው ከወጣ በኋላ የፌስቡክ አካውንቱንም ሆነ ኢሜይል አድራሻውን ፓስወርድ በቀላሉ መቀየር ይቻላል፡፡ የኢሜይል ፓስወርድ ከተቀየረ በቀላሉ በኢሜይሉ የተከፈተውን ፌስቡክ ፓስወርድ መቀየር ቀላል ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ብዙ ተከታይ ያላቸው የፌስ ቡክ ፔጆች እና አካውንቶች ሀክ ተደርገው መረጃ የሚበረበርበት እና የግለሰቡ አቋም ያልሆኑ እንዲሁም ግጭት ቀስቃሽ መልእክቶች የሚለቀቁበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ በቅርቡ እንኳን የአንድ አክቲቪስት ፌስቡክ ገጽ ሀክ የተደረገው ከቴሌ ስልኩ ወጥቶ እና ፓስወርድ ተሰርቆ ነው የሚል መረጃ በዚሁ በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የነበረ ሲሆን ከቴሌ በእርግጥ መስመሩ ወጥቷል ወይስ አልወጣም የሚለው በማስረጃ የሚጣራ ሆኖ ነገር ግን የሞባይል መስመር አዘጋግ እና እንደገና አወጣጥ ላይ የተለየ አሰራር ቴሌ ካልተከተለ ይህ አይነት የሀኪንግ ችግር ሊኖር እንደሚችል አረጋጋጭ ነው፡፡

4/ ማጠቃለያ
የሞባይል ኔት ወርክን የሚጠቀሙ እና ከስልክ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች ወደፊት ከአሁኑ በብዙ እጥፍ እንደሚጨምሩ የሚጠበቅ እውነታ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቴሌ እጅግ ጥብቅ የሆነ የሚስጥር አያያዝ እና የሚስጥር ስርቆት በሮችን የሚዘጋ አሰራር የመዘርጋት እንዲሁም ሲም ካርድ የሚሸጥበትን፣ የሚዘጋበትን እና እንደገና የሚከፍትበት ስርአት ክሮስ ቼክ አፕ እንዲኖረው ማድረግ ይገባዋል፡፡ ከሌሎች አገሮችም ልምድ መውሰድ እና አሰራሩ በራሱ ሰራተኞች ጭምር የማይናጋበትን መንገድ ቴሌ ካላዘጋጀ መጪውን የቴክኖሎጂ ትስስር ማሳካት አይቻልም፡፡ የባንኮችም የሰውን ገንዘብ ጠብቆ የማኖር፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፋይናንስ ስርአቱ ጤናማ ታማኝ ቀልጣፋ እንዲሆን የማድረግ ሀላፊነታቸው ተስተጓጉሎ ባለበት እንዲረግጥ ስለሚያደርገው ስጋቱን ከግምት ያስገባ አዲስ መንገድ ማዘጋጀት አለባቸው፣ ሰራተኞቻቸውም ከቴሌ ሰራተኞች ጋር ጭምር ተባብረው ሞባይል መስመር ጋር ያሉ የባንኩን መሰናክሎች በማለፍ ተባባሪ የሚሆኑበትን እድል የሚዘጋ አሰራር መፍጠር አለባቸው፡፡ ዜጎችም በስማቸው የሞባይል መስመር አውጥቶ ለሌላ ሰው አለመስጠት፣ በሞባይል መስመር ላይ የተለየ ነገር ሲከሰት ለቴሌ እና ለባንክ ቶሎ ማሳወቅ፣ ከማያውቁት ድንገተኛ ሰው ስልክ አለመግዛት እና በመግዛት ወንጀለኞች እንዲጠቀሙ በተዘዋዋሪ ከማድረግ መቆጠብ፣ የወደቀ መስመር አንስቶ ከመጠቀም ይልቅ ለፖሊስ የማስረከብ ልምድ ማዳበር ከብዙ ውጣወረዶች እንዲድኑ እንደሚያደርጋቸው ሊያውቁ ይገባል፡፡ ለምሳሌ አንዲት አራስ በወንጀሎኞች የተገደለን ሰው ሲም ካርድ ታክሲ ውስጥ ተጥሎ አግኝታ ቀፎዋ ውስጥ አስገብታ በፍ/ቤት ፈቃድ በተደረገ የቴሌ ኔት ወርክ ክትትል ተይዛ ህጻን ልጅ ይዛ ጉዳዩ እስከሚጣራ ፖሊስ ጣቢያ ለቀናት ቆይታለች፡፡
/note:- ለጽሁፉ ደጋፊ የሆኑ actual የቅርብ ጊዜ ኬዞች መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም ፅሁፋን ላለማርዘም አልተካተተም/

Want your practice to be the top-listed Law Practice in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Website

Address


Addis Ababa

Opening Hours

Monday 09:00 - 23:00
Tuesday 09:00 - 23:00
Wednesday 09:00 - 23:00
Thursday 09:00 - 23:00
Friday 09:00 - 22:00
Saturday 09:00 - 06:00