Ethiopian Human Rights Commission
05/05/2026
#ሶማሊ፦ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ትምህርት የማግኘት መብት አተገባበርን አስመልክቶ የተካሄደ ምክክር..
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሶማሊ ክልል በተመረጡ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት መብት አተገባበርን አስመልክቶ ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ መጋቢት 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በጅግጅጋ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል። በውይይቱ ከሶማሊ ክልል ትምህርት ቢሮ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች፣ ሴቶችና ሕፃናት፣ አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮዎች እንዲሁም ከተለያዩ የወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ኢሰመኮ የትምህርት መብት በዓለም አቀፍና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች የተሰጠውን ጥበቃ ጨምሮ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የመብቱ አተገባበር ላይ ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በውይይቱ በከፍተኛ ንፋስ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባት እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታን ማስፋፋት እንዲሁም የመምህራንን ዕውቀት እና ክህሎት ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው ስልጠና መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም ተንቀሳቃሽ እና አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋትን ጨምሮ ከአርብቶ አደሩ የኑሮ ዘይቤ ጋር የሚጣጣሙ የትምህርት ስልቶችን መቀየስ አጽንዖት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች አርብቶ አደሮች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በዘላቂነት ለመፍታት በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢሰመኮ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ኃላፊ ሃዊ አስፈው፣ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት መብትን ለማረጋገጥ ከማኅበረሰቡ የኑሮ ዘይቤ ጋር ማጣጣምና ተደራሽነቱን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም የመሠረተ ልማት ችግር እና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉና የመፍትሔ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።
🔗 https://ehrc.org/?p=37559
🇪🇹
በነጻ የስልክ መስመራችን 7307 ላይ በመደወል የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አቤቱታ ማቅረብ ወይም ጥቆማ መስጠት ይችላሉ።
25/04/2026
6ኛው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት (Human Rights Moot Court) ውድድር ተጠናቀቀ..
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበረው 6ኛው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት (6th National High Schools Human Rights Moot Court Competition) ውድድር ሚያዝያ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተካሄደ የፍጻሜ ውድድር ተጠናቋል፡፡ ውድድሩ ከጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሎች እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በ12 ክልሎች እና 2 ከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ 91 ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 182 ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል።
በክልሎች እና በከተማ አስተዳደር ደረጃ በተካሄደው የምስለ ችሎት ውድድር ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ 8 ቡድኖች ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት የሩብ እና የግማሽ ፍጻሜ ሀገር አቀፍ የቃል ክርክር ውድድር ከሚያዝያ 12 እስከ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. ሲያደርጉ ቆይተው የፍጻሜ ውድድር አድርገዋል፡፡
በፍጻሜ ውድድሩ ተማሪ መርስን ተፈራ እና ተማሪ ቦንቱ ታደሰ ከአዲስ አበባ ከተማ እቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ተማሪ ይዲድያ ብሩክ እና አናቤል ነብዩ ከደብረብርሃን ከተማ ሀይሌ ማናስ አካዳሚ አመልካችና ተጠሪን ወክለው የቃል ክርክራቸውን አካሂደዋል። በዚሁ መሠረት:-
ተማሪ መርሰን ተፈራ እና ቦንቱ ታደሰ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት የፍጻሜ ውድድሩ አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡
ተማሪ አናቤል ነብዩ ከደብረብርሃን ከተማ ሀይሌ ማናስ አካዳሚ የውድድሩ ምርጥ የቃል ተከራካሪ በመሆን ያሸነፈች ሲሆን፤
ተማሪ ኪብሮን ነጻነት እና ተማሪ ዲኒያ ናስር ከሸገር ከተማ ሒል ቶፕስ አካዳሚ በምርጥ የጽሑፍ ክርክር አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡
የዘንድሮው ውድድር ምናባዊ ጉዳይ ትኩረቱን ያደረገው “የመማር መብት በግጭት ዐውድ ውስጥ” (The Right to Education in the Context of Armed Conflict) ላይ ሲሆን፣ የትምህርት መብትን በተለይም የትምህርት ተገኝነትን (availability) ተደራሽነትን (accessibility)፣ ተቀባይነትን (acceptability) እና ተላማጅነትን (adaptability)፤ በግጭት ዐወድ ውስጥ የትምህርት መብት መርሖችን እንዲሁም የትምህርት መብትን ከማክበር፣ ማስከበር እና ማሟላት አኳያ የመንግሥት መሠረታዊ ግዴታዎችን የተመለከቱ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች ላይ ተመሥርቷል። ይህም በግጭት ዐውድ ውስጥ የትምህርት ቀጣይነትን የተመለከቱ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎችን በማንሳት ተወዳዳሪ ተማሪዎች በመብቶቹ ዙሪያ ጥልቅ ውይይትና ንባብ እንዲያደርጉ እና ዕውቀት እንዲያካብቱ አጋጣሚ ፈጥሯል።
የምስለ ችሎት ውድድሩ በሕግና ሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች የተዳኘ እና የመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሥርዓትን የተከተለ ሲሆን፤ ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተገቢው ገለጻና አጭር ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ለውድድሩ በተመረጠው ምናባዊ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ አመልካች እና ተጠሪን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር ያደረጉበትም ነው።
በዚህ የፍጻሜ ውድድር ላይ የኢሰመኮ ኮሚሽነሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልል ትምህርት ቢሮዎች ተወካዮች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የተወዳዳሪ ተማሪዎች ቤተሰቦች እንዲሁም ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ ኢሰመኮ የወጣቶችን የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤና ክህሎት ለማሰደግ እንዲሁም አመለካከት ለመቀየር ከሚጠቀምባቸው ስልቶች መካከል የምስለ ችሎት ውድድር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በግጭት ዐውድ ውስጥ የትምህርት ቀጣይነትን ማረጋገጥ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በመፍጠር ሀገራት ከግጭት ዐውድ ውስጥና ከሰብአዊ መብቶች ጥሰተቶች አዙሪት ሊወጡ የሚችሉበት የተሻለ አማራጭ መሆኑን ተረድተው፣ ይህንኑ በውድድሩ የተለያዩ ዙሮች ላይ ለተሳተፉ ተማሪዎች፣ የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ አባላት፣ ወላጆች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ማስገንዘብ እንደቻሉ ገልጸዋል። አክለውም “6ኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር ወቅታዊ እና ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳዎችን ተገንዘቦ አስተዋጽዖ የማድረግ ዐቅም ያለው ትውልድ በማፍራት ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንድንችል ዕድል የሠጠን ነው” ብለዋል።
🔗 https://ehrc.org/?p=37324
🇪🇹
በነጻ የስልክ መስመራችን 7307 ላይ በመደወል የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አቤቱታ ማቅረብ ወይም ጥቆማ መስጠት ይችላሉ።
We are live from the Final Round of the 6th High Schools Human Rights Moot Court Competition.
Watch as top students present their final arguments on “The Right to Education in Situations of Armed Conflict.”
Join the live stream and follow the competition.
Click here to claim your Sponsored Listing.
Category
Contact the organization
Telephone
Website
Address
Headquarters: Meskel Square, On Bole Airport Road Next To Hyatt Regency Hotel
Addis Ababa