Tegulet Media and Promotion
10/04/2026
እንኳን ለጌታችንና ለመድሃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በሠላም አደረሳችሁ!
መልካም በዓል
ተጉለት ሚዲያ ፕሮሞሽንና ኤቨንትስ
01/03/2026
ምኒልክ ያችን ሰዓት
(ጋሻው ደበበ አለሙ)
▫️መነሻ ሀሳብ -ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ
▫️አርትኦት- አሰግደው ሽመልስ
የካቲት 23/ 1888 ማለዳ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት እምዬ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አድዋ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ያረጉት ፀሎት
ስብሐት ለእግዚአብሔር- ኅያው በመንበሩ
ሰላም ለዛቲ -ሃገሪትነ ቅድስት
ወሰላም ለህዝብየ- ዘይሔሉ ለምድሩ
ዘይመውት -ለክብሩ ፡፡
ምስጋና ለሕያው አግዚአብሔር
ሰላም ለዚህች -አንድ ቅድስት አገር
ሰላም ለደጉ ህዝቤ-አፈሬን ብሎ ለሚኖር
ክብር ላንተ-ሰማዕቱ የእናት የአባቴ ታቦት
ጊዮርጊስ መመኪያዬ-እንግዴህ ከፊቴ ዝመት
መንገድ ጥረግ ፈረሰኛው -ቀዳማዊው ሰራዊት
ተማርኩ ያለ አገር ሊዘርፍ-ውል አዛንፎ በለበጣ
የነገር ፈሩን ስንጨብጥ -ለሴራው ብልሐት ሲያጣ
ለጦር ልቡ ሸፍቶ -ዳር ድንበር ጥሶ ከመጣ
ፈርሐ-እግዜር የሌለው ጣሊያን -ህዝቤን በጅምላ ሲወር
በህዝቤ ተደምስሶ -አደዋ አረህ ውስጥ ሲቀር
በሟጥሽ ስር ተበትኖ -በአጋም ስራስር ሲሰባበር
እለቱ በደም ታፍኖ-ሰልስቱን በአሞራ ሲያከብር
ኪደነ-ምህረት ገሰሶ-ምንድብድብ ሸዊቶ ሜዳ
እማርክ ብሎ የመጣ -ሞቱ በአፍታ ቢረዳ
እኔ ክፉ እማይደለሁ -ልቤን ቅር እንዳይለው ነገር
መቼም ነፍሰ-እግዚሃር ነውና…
ክብር ለሃያሉ አምላክ -ቃሌን ቀድሜ ልናገር ፡፡
ቴወድሮስ ይሙት! ቃሌ ነው!!
እኔ ምኒልህ …
አይኑን ለጨፈነ ጠላት -እዝኑን ለደፈነ ጦረኛ
መልህቅ ቢያነሳ ብዬ እንጂ -ይሔ ነጭ ነውረኛ
አወድመው እንደሳት ሰደድ -እመታው እንደመጋኛ፡፡
እንዴት አይነት ጥጋብ ነው ? እንዴት አይነት መወፍነን?
ምኒልክን ለባርነት- ኢትዮጵያን ለቅኝ ግዛት
አሳብ ጠንስሶ መጅመንመን?
እንዴት አይነት ንቀት ነው -ምን የሚሉት ሰማይ ማከክ?
ጣሊያን ሱሪ የለበሰው ሐበሻን ለማንበርከክ?.....
አዬ ያገሬ ጀግና
አንጀተ ፅኑው ገበሬ
በማርያም መማፀኔን -ያገር አዋጄን ሰምቶ
ከመናገሻ እስከ ሀረር በጌምድር ተጠራርቶ
የአራት ማዕዘን -ጀግና ድፍን ኢትዮጵያ ተነስቶ
በሮቹን ባለህ ባይ ሳይኖር -ዝሪቱን ለተባይ ትቶ
ወንጭፉን ከማማ ሰቅሎ -ጦርና ጋሻ አንግቶ
ምኒልህ ጠራኝ ብሎ -በጭብጦ ተሸኝቶ
በእፍኝ ጥሬ-ከቤት ወጥቶ
ላመል ታህል በኮዳ ውሃ-ከምንጭ በቅል ጠጥቶ
ለእግሩ ከለላ ሳይኖረው -አሜኮላውን ጥሶ
ጫካውን በግር በፈረስ -ዥው አርጎት እንደኮሶ
ላገር ሟቹ ቃል ጠባቂው ይሔው አደዋ ከተመ
ለነፃነቱ እልፍ ሆኖ -ለክብሩ በአንድ ተመመ
የአብሮነት ቃልኪዳኑን -በባንዲራው ስም አተመ፡፡
እና ከዚህ በላይ -ምን ደስታ አለ?
ከህዝብና ከክብሩ- ሰው ካገሩ ከዋለ
እምነትና ጀብዱን ታጥቆ -አገሩን ብሎ ለመጣ ሰው
እስከ አፅናፍ የሚነገር -ድል ነው ፀዲቅ የሚቆርሰው፡፡
እንደ ቤተ-መቅደሱ -እንደ ሞገሩ ሽታ
እንደ ነጋሪቱ ድምፅ -መለከትና እምቢልታ
ተመስገን ያባቴ አምላክ -ልቤ ሃሴት ተሞልቷል
ሰማዕቱ በእለተ ቀንህ -ክንዴ እልፍ ጦር አንግቷል
ህዝቤ -አፎቱን ከፍቷል
ብቻ ህልም አየሁ በሰመመን…
አንጎለላ ኪዳነምህረት -ከደጅሽ የወይራ አፀድ
በቀስተዳመና ተከቦ- አንዱ ክንፍ ተቆርጦ ሲወርድ
ይሔ ሃሞተ መራር-ይሔ ልበ ተራራ
የሰው ምክር ግድ የለው-ትንሽ ለነፍሱ አይፈራ
ቀኝ እጄን እንዳላጣው- ክንዴን ገበየሁን አደራ::
ክብር ለአያቶቼ
ኢትዮጵያን ከነ-ስሟ -ከነ ክብሯ ላኖሯት
ጣሊያን ጉድጓዱ ይገባል -ዛሬም ማንም አይደፍራት።
የካሳ እልፍኝ ይታዘበኝ -ጦር ሰልጥኜ ያደኩበት
ልበ-ባህሩ ሸዋ -አባ መቻል-አባ መስጠት
ስም አልጠራም አባባ ብዬ -አይወልደኝም ሀይለመለኮት
እኔ ዳኘው ምኒልህ -ወገኔን ካሳፈርኩት !!
በቀዳማዊ ምኒልክ -በሳህለ ሥላሴ መንፈስ
በአያቴ ወንበር ዘውድ ስጭን -በጥንቶቹ አልጋ ስነግስ
እንዴት ተብሎ ቃል ቢዛነፍ-ጫፏ ይነካል አገሬ
አፍር ይሆናል እንጂ-ጠላት ይገባል መረሬ!!
እውነት ኪዳነ-ምህረት -በቀንሽ ቅጠል ሳልበጥስ
ዳዊት ከደጅሽ ደግሜ -ፀበል ጠጥቼ ሳልሰልስ
ቆመ-ብዕሴሽን ታሽቼ-ገራገራሽን ተሳልሜ
የኖርኩት የከበርኩት -ባንች እማዶለ አለሜ !
ፈገግተዋ የሚያጠግበኝ-የመኖር ውሃ ሙላቴ
እንግዲህ አንቺ ከልያት-ከፊት ቀድማለች ጣይቴ ፡፡
አሔሔ!
ኢትዮጵያዊነት ሥሙ -ሀይሉ ካድማስ የሚርቀው
የወገኔ እንኳን ጦሩ-ድምጡ ጠላት የሚንደው
ከወረይሉ እስከ ሶሎዳ - እየፎከረ የተመመው
እምቢ ብሎ እንደመጣ -የድል ጀንበር ሊያሳልፍ ነው፡፡
እንግዴህ ይህ ነው ፀሎቴ ...
ይህ ቀን -ታላቅ ነውና -
የኢትዮጵያ ሐያልነት በአደባባይ ይወሳ
ወራሪ አጥንቱ ደቆ- ከደሃ ላይ እጁን ያንሳ
አንበሳ አንበሳ ነውና- እንደትላንቱ ዛሬም ያግሳ
ጥቁርና የጥቁር ምድር- አንገቱ ቀና ይበል
የሐበሻን ጠንካራ ክንድ -አውሮጳም አምኖ ይቀበል ።
እኔ ምኒልህ
አይኑን ለጨፈነ ጠላት -እዝኑን ለደፈነ ጦረኛ
ልቦና ቢገዛ ብየ-እንጂ -ይሔ ነጭ ነውረኛ
አወድመው እንደሳት ሰደድ -እመታው እንደመጋኛ፡፡
ብቻ ህልም አየሁ በሰመመን…
አንጎለላ ኪዳነምህረት -ከደጅሽ የወይራ አፀድ
በቀስተዳመና ተከቦ -አንዱ ክንፍ ተቆርጦ ሲወርድ
ይሔ ሃሞተ መራር-ይሔ ልበ ተራራ
የሰው ምክር ግድ የለው-ትንሽ ለነፍሱ አይፈራ
ቀኝ እጄን እንዳላጣው ክንዴን ገበየሁን አደራ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Click here to claim your Sponsored Listing.
Category
Telephone
Website
Address
Bole
Addis Ababa
04