AAU - Muslim Students Union
21/04/2026
የፌደራል መጅሊስ ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ስላለው የመብት ጥሰት ከ19 ወራት ቡሃላ የመጀመሪያ ንግግራቸውን አድርገዋል። እርሳቸው እንደተናገሩት ከዶክተር ሳሙኤል እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል። የሀሩን ሚዲያ ዘገባ እንደሚያመላክተው ደግሞ ስለጨቋኙ መመሪያ የተናገሩት ነገር የለም።
አሁንም ጥያቄያችን ግልፅ ነው። መጅሊስ ሀላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ። የተበደሉ ተማሪዎች አስፈላጊው ካሳ ይሰጣቸው። ጨቋኙ መመሪያ ይሻሻል።
ጥያቄ አለን _ መልስም እንፈልጋለን!!!
AAU - Muslim Students Union
20/04/2026
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች ሕብረት ዩኒቨርስቲው በሙስሊም ተማሪዎች ላይ እያደረሰ ባለው የመብት ጥሰት ዙሪያ የትምህርት ሚኒስቴር አስቸኳይ የሕግ ጣልቃ ገብነት እንዲያደርግ ጠየቀ ! ! !
--------------------------------------
ሚያዚያ 12 / 2018 ዓ.ል
--------------------------------------
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሙስሊም ተማሪዎችን ሰብዓዊ መብት በመጋፋት የሐይማኖት ነፃነት መብታቸውን የሚጋፋ መመሪያ አውጥቶ ላለፉት 19 ወራት ተማሪዎችን ለእንግልት እና ለስነ-ልቦና ጫና ሲዳርግ እንደቆየ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎም ሙስሊም ተማሪዎች የተፈፀመው የመብት ጥሰት ቆሞ ተማሪዎች ነፃነታቸው ተከብሮላቸው ይማሩ ዘንድ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ቢያደርጉም አሻፈረኝ በማለት ለተማሪዎቹ ቅሬታ ጆሮዳባ ልበስ ብሏል።
የውይይት በር መዘጋቱ የመብት ጥሰቶቹ ተደጋግመው እንዲፈፀሙ መደላድል ከመስጠቱ ባሻገር ተማሪዎችን አላስፈላጊ ለሆኑ ጫናዎች እየዳረገ ነው። ይህ በቶሎ ቆሞ ችግሮች በውይይት ይፈቱም ዘንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች ሕብረት በዛሬው እለት ለትምህርት ሚኒስቴር ደብዳቤ አስገብቷል። በደብዳቤውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፦
1ኛ፦ የዩኒቨርስቲው አድሏዊ መመሪያ የዜጎችን የመማር መብትና ሕገ- መንግስታዊ ነፃነት በሚፃረር መልኩ የወጣ በመሆኑ፤ በአስቸኳይ እንዲነሳና መመሪያው እንዲሻሻል ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥ።
2ኛ፦ ዩኒቨርስቲው ለደህንነት ፍተሻ ያቀረብናቸውን ዘመናዊ እና ሐይማኖታዊ መብትን የማይጋፉ አማራጮች ተግባራዊ እንዲያደርግ ግፊት እንዲደረግ
3ኛ፦ ኒቃብ ለባሽ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ሳይሰተጓጎሉ እኩልነታቸው ተከብሮ እንዲማሩ ክትትል እንዲደረግ
ተጠይቋል።
ጥያቄ አለን _ መልስ እንፈልጋለን !
AAU - Muslim Students Union
31/03/2026
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሙስሊም ሴቶች በዩኒቨርሲቲው እየደረሰባቸው ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ድምፅ ይሆኗቸው ዘንድ በEBC እና ፋና ዋና ፅ/ቤት በመገኘት አቤቱታ አቀረቡ ! ! !
--------------------------------------------
መጋቢት 22 / 2018 ዓ.ል
--------------------------------------------
ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ከሆኑ ቡሃላ የሙስሊም ተማሪዎችን ሒጃብ (ኒቃብ) የመልበስ ሰብዓዊ መብት የሚከለክል ኢ- ሕገመንግስታዊ መመሪያ ወጥቶ ተማሪዎች ለመጠነ ሰፊ እንግልት መዳረጋቸው የሚታወቅ ነው። ይህንንም ተከትሎ ላለፉት 18 ወራት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች የተደረገ ሲሆን ባለፉት ሳምንታት ውስጥ በማህበራዊ ሚዲያ በተደረገ ዘመቻ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ሐብት የሆኑት እነ EBC: FANA እና ሌሎች ሚዲያዎች የተማሪውን ድምፅ እንዲያስተጋቡ፤ ዩኒቨርሲቲውን እና አመራሩንም ተጠያቂ እንዲያደርጉ ሲጠየቅ ነበር።
ሆኖም ምላሽ ባለመገኘቱ በዛሬው እለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በሚዲያዎቹ ጽ/ቤት በመገኘት ሚዲያዎቹ ሚዛናዊ እና ፍትሐዊ ዜናዎችን በመስራት እና ዘገባዎችን በማውጣት በሙስሊም ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ስላለው የመብት ጥሰት ድምፅ ሆነው ሀላፊነታቸውን ይወጡ ዘንድ ጠይቀዋል።
በአላህ ፈቃድ መሠል እንቅስቃሴዎች በሙስሊም ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እስኪቆም ድረስ የሚቀጥል ይሆናል። በቀጣይ የሚኖሩ እንቅስቃሴዎችን እና ውጤቶችንም የምናሳውቃችሁ ይሆናል።
ጥያቄ አለን: ዛሬም ነገም!
ጥያቄ አለን: ፍትሐዊ መልስ እስኪመጣ!!
ጥያቄ አለን: ቢሮ ውስጥም በአደባባይም!
AAU - Muslim Students Union
24/03/2026
Gaaffii Qabna !
በዳይ በደሉን እስኪያቆም፤ ጨቋኝ ጭቆናውን እስኪገታ፤ ፍትሕ ሰፍኖ ተበዳይ እስኪካስ ጥያቄ አለን።
We Have A Question
We Want An Answer !!!
ጥያቄ አለን ! ! !
AAU - Muslim Students Union
ጥያቄ አለን፦ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት የተገነባው አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙስሊም ተማሪዎችን መብት የሚጥስ መመሪያ ለምን እንዳወጣ ጥያቄ አለን! መማር ማስተማሩ በሰላም እየሄደ ባለበት ድንገት ተነስቶ ሒጃብ ለባሽ ሙስሊም ተማሪዎችን በር ላይ፤ ካፌ ውስጥ ብሎም በመማሪያ ክላስ ለምን ሊያንገላታ እንደፈለገ ጥያቄ አለን!!
ጥያቄ አለን፦ በሕዝብ ሐብት የተቋቋሙ የሕዝብ ሚዲያዎች (EBC: Addis media network ወዘተ...) ፤ ለሕዝበ ሙስሊም ድምፅ ይሆኑ ዘንድ የተቋቋሙ ሚዲያዎች ፤ ስለ ሰብዓዊ መብት ይገደናል የሚሉ አለምአቀፍ ሚዲያዎች (DW, BBC, Anadolu, TRT, Al-jezira etc...) ብሎም በሀገር ውስጥ ያሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች (ቲክቫህ፣ ATC etc..) እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ሁሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ተማሪዎች ላይ ከአመት በላይ ሕገ-ወጥ መመሪያን ተገን ያደረገ የመብት ጥሰት ሲካሄድ ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን ለምን እንዳልሰጡ ጥያቄ አለን!!!
ጥያቄ አለን፦ ስለ ሴቶች ተብሎ በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ የተቋቋመው የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር የሙስሊም ሴቶች መብት ሲጣስ ለምን ዝም እንዳለ ጥያቄ አለን። ስለ ሰብዓዊ መብት ተብሎ የተቋቋመው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ተማሪዎች ሰብዓዊ መብት ሲጣስ አስቸኳይ እርምጃ ስለምን እንዳልወሰደ ጥያቄ አለን።
መልስም እንፈልጋለን። መልስ ፍትሐዊ መልስ እስኪሰጡም በሁሉም መንገድ እንጠይቃለን። መብታችን ስለሆነ። ተቋማቱ የእኛም ጭምር ስለሆኑ። መጠየቅ ግዴታችን ስለሆነ። መመለስም ግዴታቸው ስለሆነ።
ለመጠየቅ ዝግጁ ናችሁ? ለመጠየቅ ዝግጁ ነህ? ለመጠየቅ ዝግጁ ነሽ?
17/03/2026
ዓለም አቀፍ የኢስላሞፎብያ መከላከያ ቀን (March 15, 2026) !
በተባበሩት መንግስታት መሪነት በአለምአቀፍ ደረጃ እየተሰራጨ ያለውን ሙስሊም ጠልነት ለመግታት ያለመ ፕሮግራም በድርጅቱ አዳራሽ በየአመቱ March 15 ላይ ይካሄዳል። ከትላንት ወዲያም ቀኑ ነበርና በአዳራሹ የተገኙ ሰዎች መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። እኛም በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙስሊሞችን የሚያገል መመሪያ ከማውጣት ጀምሮ ሙስሊም ተማሪዎች ላይ የሚፈፅመውን በደል ታሳቢ በማድረግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ካስተላለፉት መልዕክቶች ጥቂቱን ለማስፈር ወደድን። መልዕክቱ በቀጥታ ለዩኒቨርሲቲው የተላለፈ ይመስላልና እንደወረደ አንብቡት።
መልዕክት 1:-
"...አድሎአዊ ትረካዎች በስልጣን ላይ ባሉ አካላት ሲስተጋገቡ፣ ጥላቻ እንደ ተለመደ ነገር ይቆጠራል። የተዛቡ አመለካከቶች (Stereotypes) ሳይታገሉ ሲቀሩ፣ ወደ ፖሊሲነት ይጠነክራሉ። ፍርሃት ውሳኔዎችን እንዲመራ ሲፈቀድ ደግሞ ኢፍትሃዊነት ይከተላል...”
ዋና ጸሐፊው አክለውም በእያንዳንዱ ሰው፣ በሁሉም ቦታ ለሚገኝ እኩልነት፣ ሰብአዊ መብትና ክብር” አዲስ ቁርጠኝነት እንዲኖር አሳስበዋል፤ እንዲሁም እየናረ የመጣውን ሙስሊም ጠልነትና ለሙስሊሞች ያለ ክፉ አመለካከትን ማዕበል ለማጥፋት እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥሪ አቅርበዋል።
እኛም የሚከተለውን እንላለን:- በስልጣን ላይ ባሉ ሰዎች አድሏዊ ትረካ፣ በእነርሱ የተዛባ አመለካከት እና በሌሎች ፍርሐት የወጣው አድሏዊ መመሪያ የሚሻርበት ጊዜ አሁን ነው። ለዚያ ደግሞ የእኛ የተስተካከለ ግንዛቤ፤ የተቀናጀ አካሄድ እና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። በዚህም የተስተካከለ እና ፍትሐዊ ከባቢን ለመጪው ትውልድ የምናወርስ ይሆናል።
13/03/2026
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በግቢው የሚገኙ ሙስሊም ተማሪዎች ፊርማቸውን አሰባስበው ላስገቡት የመብት ጥያቄ አሰራርን የጣሰ፤ አሳፍሪ እና ለተማሪዎቹ ቦታ እንደሌለው የሚያሳይ ምላሽ ሰጠ!
በቁጥር 1,141 የሚሆኑ፣ ማንነታቸው በውል የሚታወቅና በዩኒቨርሲቲው መዝገብ ላይ ያሉ ተማሪዎች፤ መብታችን ይከበር ብለው ያቀረቡትን አቤቱታ አስተዳደሩ በፌዝ መልሶታል። በደብዳቤው ላይ በጥቁር ስክሪቢቶ ስርዝ በማድረግ "እንደዚህ የሚባል ክበብ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አናውቅም። ተመላሽ ይደረግ!" የሚል አሳፋሪ ምላሽ ሰጥቷል። አስተዳደሩ የሰረዘው የወረቀት ላይ ፅሁፍ ሳይሆን የ1,141 ተማሪዎችን ህያው ድምፅ ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ፒቲሺን ፈርመው ሲያስገቡ የመጀመሪያቸው አይደለም። ከበፊት ጀምሮ ቅሬታ ሲኖራቸው ከዩኒቨርሲቲው ጀምሮ አስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ድረስ አስገብተው ያውቃሉ። አሁን ላይም የተፈረመውን ፒቲሽን አልቀበልም ብሎ የመለሰው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ የሐይማኖት ተቋማት ድረስ ገብቷል።
በሁለተኛ ደረጃ 1141 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ተማሪዎች መብታችን ተነካ ብለው ስለመብታቸው ቅሬታ ያስገቡት በክበብ ደረጃ ተደራጅተው አይደለም። ክበብ ነኝ ብሎ ያልሄደን አካል እንዲህ የሚባል ክበብ አላውቅምና ምላሽ አልሰጥም ማለት ከግንዛቤ የራቀ ነው።
መጅሊስን ጨምሮ የሚመለከታችሁ የመንግስት አካላት፤ ዩኒቨርሲቲው የያዘው ይህ ግትርና ተማሪን አግላይ አካሄድ እንዲቆም፣ እንዲሁም የሙስሊም ተማሪዎችን መብት የሚያከብር መመሪያ እንዲያወጣ የበኩላችሁን እንድታደርጉ እንጠይቃለን።
እኛ "ክበብ" አይደለንም፤ እኛ የዚህ ተቋም ግማሽ አካል የሆንን ተማሪዎች ነን! ጥያቄያችን ህያው ነው፣ መልስም እንፈልጋለን!
ጥያቄ አለን!
መልስ እንፈልጋለን!
Click here to claim your Sponsored Listing.
Category
Contact the place of worship
Telephone
Website
Address
Addis Ababa