Yetneberk Tadele

Yetneberk Tadele

Share

Photos from Yetneberk Tadele's post 01/06/2026

ባለፈው ሰሞን አንዲት የአራተኛ አመት የፋርማሲ ተማሪ በመመረቂያ አመቷ የትምህርት ቤት ክፍያ አጣሁ በማለት ራሷን አጠፋች የሚል ዜና አየሁ:: በወቅቱ የኢኮኖሚ መንገራገጭ ሳቢያ ችግር ላይ የወደቁ: ያሰቡበት መድረስ አልቻልንም የሚሉና ጊዝያዊ ችግራቸውን ዘላለማዊ አድርገው ያሰቡ ብዙ ወጣቶች በአሳዛኝ ሁኔታ በለጋ እድሜያቸው ይህችን ምድር በገዛ ፈቃዳቸው ተሰናብተዋል:: ዛሬም ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው በሶሻል ሚዲያ ለሞት ሲያንገራግሩ ይሰማል። እኔ በሁሉም ላይ ለመፍረድ ፍላጎት የለኝም:: ነገር ግን እኔ እንደ እናንተ አስቤ በነበረ ኖሮ ገና በአስራዎቹ እድሜዬ ራሴን አጥፍቼ ተዘንግቼ ነበር…..

የ12ኛክፍል ማትሪክ የወሰድኩት በ16 አመቴ ነበር:: አባቴ የመፈተኛ አመት ላይ ምንም ዝግጅት አለማድረጌን ሲመለከት ደግመህ ተማር አለኝ:: እምቢ አልኩት:: ከቤት አባረረኝ:: የጓደኛዬ ቤተሰቦች ጋር ተጠግቼ ማትሪክ ተፈተንኩ:: አባቴ እንደፈራው ውጤት ሳይመጣልኝ ቀረ:: አንድ አጎቴ ይሰራበት የነበረ የነዳጅ ማደያ ተቀጥሬ እያጠናሁ ድጋሚ ለመፈተን ማጥናት ስጀምር የማደያው ባለቤት ወዲያው አባረረኝ:: መሄጃ ጠፋኝ:: ገዳም ልገባ ጠፍቼ ሄድኩ:: ሁለት ወር ቆይቼ ልጅ ነህ ብለው አሰናበቱኝ::

የት ልሂድ? አንድ የረሳሁት አጎት ሩቅ ሀገር እንዳለኝ ትዝ አለኝ:: ትራንስፖርት እየለመንኩ ከዝያም የ12 ሰአት የእግር መንገድ 20 ወንዝ ስችል እየዋኘሁ ሳልችል ወደ ፈለገበት ይግፋኝ እያልኩ ረሀብ እየጠበሰኝ እንደ ማስቲሽ እግር ላይ የሚጣበቅ ጭቃ አቆራርጬ ደረስኩ:: እዚህ ጋር መሞት እችል ነበር:: የምሄድበትን አላውቅም ድካምና ረሀብ አንገላቶኛል፤ ተስፋ የለኝም፤ ነገ ምን እንድምሆን አላውቅም:: እዝያው ወንዝ ውስጥ ስምጥ ፀጥ ብዬ ብቀር እችል ነበር::

እዝያ ጭልም ያለ ጫካ ውስጥ በማላውቀው ባህልና ቋንቋ ውስጥ ጥቂት ወራት ቆየሁ:: መኪና የለም: መብራት የለም: ቴሌቭዥን የለም፣ ስልክ የለም፤ አዲስ ነገር የለም:: ዥውው ያለ ገጠር:: እንዳልመለስ ያንን የመጣሁበትን የስቃይ መንገድ ያንን ወንዝ ፈራሁ:: ቆይ ውሀው ይጉደል እየተባልኩ እዝያው ሰነበትሁ::

በዚህ መሀል አንድ ጽናቴን ያየ የትምህርት ቢሮ ሀላፊ ታሪኬን ሰምቶ አዘነልኝና ያለቋንቋ ፈተና ደባብቆ መምህርነት ስልጠና እንዳገኝ አመቻቸልኝ:: ..... እፎይ!!

ኮሌጁ ስደርስ ግን ውጤቴ ቢያስገባኝም እድሜዬ ለመምህርነት ቁመቴም ለሰሌዳ እይመጥንም በማለት ለሚቀጥለው አመት ተመለስ ተባልኩ:: ... ወደ ማን እመለሳለሁ? በምን ሳንቲም እመለሳለሁ? ..... ለተማሪዎች ዶርም ተሰጠ የካፌ ካርድ ተስጠ:: እኔ በረሀብ እየተቆራመድኩ በብርድ እየተጠበስኩ ሁለት ቀን ከቢሮው ደጅ እያደርኩ ዲኑን በለቅሶ እያስቸገርኩ ቆየሁ:: እግዜር ይስጠው ተለመነኝ። ተመርቄ መምህር ሆንኩ::

ሌላ የሚቀበለኝ ስለሌለ እዝያው የላከኝ ቦታ ተመልሼ አንድ እመት አስተማርኩ:: ከዝያ በላይ አልቻልኩም:: ወደ ትውልድ ስፍራዬ ተመልሼ በመምህርነት ቅጠሩኝ ብዬ እመለከትኩ:: ቋንቋውን እችላለሁ: እንግሊዘኛም በደንብ ማስተማር እችላለሁ አልኳቸው:: ካለህበት ቦታ መልቀቅያና መሸኛ አምጣ አሉኝ:: ጊዜ ሳላጠፋ አመጣሁ:: …..ሳቁብኝ:: ችግሩ ከስምህ ነው ስምህንም ቀይረው ብለው አፌዙብኝ:: ደነገጥኩ:: ቅስሜ ተሰበረ:: ተስፋ ቆረጥኩ:: እዚህም ጋ መሞት እችል ነበረ:: ዘመድም ሀገርም አጣሁ፣ ጨላለመብኝ::

አፈር ግጬ አፈር በልቼ እንደገና ተማርኩና ስጨርስ ወደ አዲስ አበባ አመራሁ:: እዝያም ገብቼ እንዳይደላኝ ብዬ ቀን እያስተማርኩ ማታ እየተማርኩ ተመረኩ:: በተመረቅሁበት ሙያ ስራ አግኝቼ ተቀጠርኩ:: ብዙም እልቆየሁ ከአንዴም ሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራ ተፈጸመብኝ:: ከባለስልጣናት እስክ ፖሊስ ተደራጁብኝ:: በስለት ተወግቼ ተጣልኩ:: የቀጠረኝ ድርጅት እንኳ የት ወደቀ ብሎ ሳይፈልገኝ ጅብ ይብላው ብሎ ሸሸኝ፣ ሞቴን አድበስብሶ አለፈው:: ጉዳዩን የሚያውቁ የሙያ አጋሮቼም ሰምተው እንዳልሰሙ ሆኑ:: ሀገሬን ጥዬ ተሰደድኩ:: .... ሌላ የጭንቀት ህይወት አሳለፍኩ::

ሳልሞት ቀረሁ:: እግዚአብሔርም አልገደልኝም: የዛቱብኝም ሊገድሉኝ ሳይችሉ ቀሩ። እኔም ተስፋ ቆርጬ ነፍሴን አላጠፋሁዋትም::

ቀን ያልፋል፣ ጊዜ ይለወጣል፣ ኢኮኖሚ ይሻሻላል፣ ተስፋ አስቆራጮች ሁሉ ያልፋሉ፣ .......ትልቁ ነገር አንዲት ነፍስን ጠብቆ በትዕግስትና በጽናት መጓዝና ነገን ተስፋ ማድረግ መቻል ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ፈጣሪ ያለ ምክኒያት አልፈጠረኝም ብሎ ማመን ነው።.....

እኔ ዛሬ ያ ሁሉ መከራና ስቃይ አልፎ ከምፈልገው በላይ ብቻ ሳይሆን መሸከም ከምችለው በላይ ተደርጎልኝ፣ በፍቅርና በትዳር ተሰብስቤ፣ በልጆች ተከብቤ፣ በልጅነቴ ተመኝቼ ያጣሁትን ትምህርት አለም አለኝ ብላ ከምትኮራባቸው ታላቅ የትምህርት ተቋም ውስጥ እየተማርኩ፣ ዘመኑ ከፈጠራቸውና የቴክኖሎጂ የመጨረሻው የተባለለትን መኪና እያሽከረከርኩ፣ ፈጣሪዬን እያመሰገንኩ በደስታ እኖራለሁ። ነገ ከዛሬ በእጅጉ የተሻለ ሰው ሆኜ ማን ያውቃል ሀገሬንና ህዝቤን እንደገና ለማገልገል እበቃ ይሆናል። እኔስ ባልበቃ ልጆቼ......

ተስፋ ቆርጬ ቢሆን ኖሮስ? ሞቼ ቢሆን ኖሮስ?......
እንኳን ፈጣሪ በሰጠኝ ህይወት ይቅርና ራሴ ባቀድኩት ነገር እንኳ ተስፋ ቆርጬ ወደ ሁአላ ተመልሼ አላውቅም!!..... ወጣቶች ሁሉም ነገር በነበረበት አይቀጥልም እና ዛሬ በዋላችሁበትና ባደራችሁበት ልክ ብቻ እያሰባችሁ በነገ ላይ ተስፋ አትቁረጡ! በነፍስ አይጨከንም። ነገን ማን ያውቃል?...ማንም!!! ከመኖር ተስፋ አለ! ካለ መኖር ምን አለ? - ምንም የለም!!

Want your business to be the top-listed Media Company in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Address

Addis Ababa