Yonas Tade
07/24/2026
ጌታዬ መድሃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ:- የምትኖበት ሃገር ወዴት ነው? ማደሪያህስ? የዘላለም መኖሪያህ ምስራቅ ነው ወይስ ምዕራብ? ስሜን ነው ወይስ ደቡብ? የአድማስህስ ስፋት? የክብርህስ ከፍታ መለኪያው ምን ይሆን? መድሃኒቴ ሆይ:- ቤተልሄም ተወለድክ ብለውኝ ወዳዚያ ፈጥኜ ብወጣ ስደት ግብጽ ወርደሃል አሉኝ። ግብጽ ልፈልግህ ብወርድ ናዝሬት ወጥተሃል አሉኝ። ወደዛ አቅንቼ የናዝሬቱ ኢየሱስ ወዴት ነው ብዬ ብጮህ ልትጠመቅና ሰማይ ልትከፍት ሄኖን ዮርዳኖስ ወርደሃል አሉኝ። ወደዚያ ፈጠኜ ብደርስ ለጾም ገዳም ወርደሃል አሉኝ። ኢያሪኮ ቆሜ ብጠብቅህ ለድሆች ወንጌልን ትሰብክ ዘንድ፣ የተጠቁትን ታድን ዘንድ፣ የተወደደችውን የጌታን ዓመት ትሰብክ ዘንድ ፣ለጽዮን አልቃሾች በአመዳቸው ፈንታ አክሊልን ትሰጥ ዘንድ፣ ኢየሩሳሌም፣ ቤተሳይዳ፣ ገሊላ ወርደሃል አሉኝ። ትንሽ ቆይቼ ባህሩ ዳር ቆሜ ስጠብቅህ ጌርጌሴኖን መቃብር ስፍራ አንድ ወጣት ልትፈውስ ተሻግረሃል አሉኝ። ኢየሩሳሌም ወርጄ ብጠብቅህ በጭፍራ ተከበህ ይሰቀል! ይሰቀል! እየተባልክ ወደ ተራራ እንደወሰዱህ ሰማሁ። አርፍጄ ከነጋ ብመጣ መስቀል ላይ ሰቅለውሃል አሉኝ። ወደ ቀራንዮ ስሮጥ ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው መቃብር እንዳስተኙህ ስማሁ። ሰንበቱን አሳልፌ ወደ መቃብር ብሮጥ መነሳትህን ሰማሁ። ከአትክልቱ መቃብር አጠገብ ተደፍቼ አልቅሼ ተነስቼ ወደ ቢታኒያ ብሮጥ አርገሃል፣ በአባትህ ቀኝ ተቀምጠሃል አሉኝ። ከተራራው ስወርድ አቤቱ በልቤ ውስጥ አገኘሁህ። በነፍሴ ውስጥ ስትራመድ በዋሻው ልቤ ውስጥ ተቀምጠህ አገኘሁ። ሰማይ የማይችልህ እኔ ቤት ተገኘህ። ዛሬም በረት መተኛት አልሰለቸህም። መቃብር ማደር አልታከተህም! እንዴት ልቤ ውስጥ እንዴት? መልስ አልሰጠኸኝም። ነገር ግን አሁንም ከእኔ ጋ አለህ። በውስጤ ዓለም አለህ!
እባካችሁ ለሌሎች አካፍሉት
ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም
ለክለሳ ተመልሰህ አትመጣምና ዛሬን በጎ ተግባር ፈፅምበት::
Click here to claim your Sponsored Listing.