AWRA AMBA
21/04/2026
እኩልነት በተግባር የሚተረጎምባት የአውራ አምባ መንደር!
ለዘመናት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች በጾታ፣ በሀብትና በማህበራዊ ደረጃ በሚገነቡ የልዩነት ግንቦች ተከፋፍለው ቆይተዋል። ይህ አይነቱ አድልዎ የሰፈነበት አኗኗር አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች በማድረግ፣ የሰው ልጅ ሊኖረው የሚገባውን ተፈጥሯዊ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ገድቦት ቆይቷል።
ነገር ግን ይህንን የአድልዖና የልዩነት ስርአቶችን በመናድ፣ የአውራ አምባ ማህበረሰብ በጾታ እኩልነት፣ በጋራ መከባበርና በፍትሃዊ የስራ ክፍፍል ላይ የተመሰረተ አዲስ የህይዎት አቅጣጫን ቀይሶ በተግባር እያሳየ ይገኛል።
በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ "እኩልነት" በየእለቱ በተግባር የሚታይ እሴት ነው። ሴቶችም ሆኑ ወንዶች በስራ፣ በሀብት ክፍፍል እና በውሳኔ ሰጪነት ላይ ያላቸው ሚና እኩል መሆኑ፣ ማህበረሰቡን ሰላማዊ እና ፍትሃዊ እንዲሆን አድርጎታል።
በአውራ አምባ ስራ የሚለካው በችሎታ እንጂ በጾታ አይደለም። ወንዶች ሴቶች የሚሰሯቸውን ስራዎች፣ ሴቶችም ወንዶች የሚሰሯቸውን ስራዎች ያለ አድልዖና ያለ ይሉኝታ ይከውናሉ። ይህ መከባበርና መደጋጋፍ በቤተሰብ ውስጥ ሰላምን ከማስፈኑ ባለፈ፣ ልጆችም ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ፍትሃዊነትንና የሰው ልጅን ክብር ተረድተው እንዲያድጉ ትልቅ መሰረት ሆኗቸዋል።
ይህ በውይይትና በጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተው አኗኗራቸው፣ በተለይም በባልና ሚስት መካከል ያለው ግልጽነትና እኩልነት ለማንኛውም ማህበረሰብ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።
በአጠቃላይ፣ የአውራ አምባ ተሞክሮ የሚያሳየን እኩልነት የአንድ ወገን ጥቅም ሳይሆን፣ የሁለቱም ጾታዎችና የጠቅላላው ማህበረሰብ የእድገት ቁልፍ መሆኑን ነው።
ሙሉ ቪዲዮውን ለመመልከት https://youtu.be/J5Awmg7X33w
14/04/2026
ሃሜትን ማስወገድ ይቻላል?
ሃሜት በሰው ልጆች መካከል ጥላቻን በመዝራት ለዓመታት የዘለቀን ጓደኝነት የሚንድ፣ በግለሰቦች መካከል አለመግባባትን በመፍጠር በጥላቻ መንፈስ እንዲተያዩ መንገድ የሚጠርግ እና በጥቅሉ ማህበረሰቡን ለማይወጣው ማህበራዊ ቀውስ የሚዳርግ ሲሆን ይህ ማህበራዊ በሽታ በባለትዳሮች፣ በቤተሰብ፣ በጎረቤትና በጓደኝነት መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት በማሻከር፣ የሰው ልጅ በፍቅር፣ በሰላምና በመተማመን መኖር እንዳይችል እንቅፋት ይሆናል።
ሃሜትን በግልጽ ውይይት በመፍታት ሰላማዊ ኑሮን ማስቀጠል እንደሚቻል ታውቃላችሁ?
ብዙዎች ሃሜትን እንደ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ቆጥረው ማስወገድ እንደማይቻል ቢያምኑም፣ የአውራ አምባ ማህበረሰብ መስራች የሆነው ዙምራ ኑሩ ግን ሃሜትን በውይይት በመፍታት ሰላማዊ ኑሮን ማስቀጠል እንደሚቻል በተግባር ያስተምራል።
ዙምራ ኑሩ ይህንን ስር የሰደደ ችግር ለመቅረፍ እንደ ዋነኛ መፍትሄ የሚያስቀምጠው ነጥብ፣ ግልጽነትና እዚያው ባለበት የመነጋገር ባህልን ማዳበር ነው። አንድ ሰው ሲሳሳት ወይም ስህተት ሲሰራ ሲታይ፣ ጉዳዩን ለሌላ ሶስተኛ ወገን ወስዶ በማማት የሰውን ስም ከማጥፋት ይልቅ ለባለቤቱ እዚያው በግልጽ መናገር ይገባል። ቁጣን አስወግዶ በፍቅር እና በፈገግታ “ይህን ነገር እንዴት አየኸው?” ብሎ መጠየቅ፣ ሃሜት ሳይወለድ እዚያው እንዲቀር በማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
ወሬን ከማመላለስ ይልቅ ግለሰቡ ስህተቱን እስኪያስተካክል ድረስ በግልጽ በመመካከር እውነትን ማምጣት የሰው ልጅ ዋነኛ ተግባር ሊሆን ይገባል። የሌላውን ሰው ሀብትና ንብረት እንደምንጠብቀው ሁሉ፣ በሃሜት ምክንያት የሚጠፋውን የሰው ስም እና ስብዕና መጠበቅም የራስን ሀብት እንደመጠበቅ ይቆጠራል።
በአጠቃላይ ሃሜት የሰውን ስም ብቻ ሳይሆን የራስን የህሊና ሰላም እና ክብር የሚያፈርስ ማህበራዊ ቀውስ በመሆኑ፣ እንደ በሽታ ተቆጥሮ ሊታከም ይገባል። ዙምራ ኑሩ እንደሚመክረው፣ እውነትን ፊት ለፊት የመናገርን መድሃኒትነት በመጠቀም የራስንና የሌላውን ሰብዕና መጠበቅ ይቻላል። ይህን የግልጽነትና የውይይት ባህል በተግባር በማዋል፣ በጥላቻና በጥርጣሬ ፋንታ ፍቅርንና መተማመንን የሰፈነበት ማህበረሰብ መገንባት የሁላችንም ድርሻ ነው።
ሙሉ ቪዲዮውን ለመከታተል https://youtu.be/Jb-RwZo5dSg
30/03/2026
"ሰርቶ ሰርቶ ሲጨርስ የሚጣለው እቃ እንጂ የሰው ልጅ አይደለም !"
በመላው አለም የሚኖሩ ዜጎች በእርጅና ወይም ደግሞ በጤና እክል ምክንያት የፈለጉትን ያክል ሳይንቀሳቀሱ፣ የጀመሩትን ውጥን ከግብ ሳያደርሱ ፣ ለወደፊት ቀጣይ ህይወታቸው መሰረት ሳይጥሉ ፣ ሰው እያለ የሚያግዛቸውና የሚረዳቸው ባለማግኘታቸው የሚበሉት ፣ የሚጠጡት ፣ የሚለብሱት አጥተው ፥ ቢታመሙ የሚታከሙበት ቸግሯቸው በየጎዳናውና በየደሳሳ መኖሪያቸው ተቀምጠው ማየት የተለመደ ጉዳይ ነው።
የአውራ አምባ ማህበረሰብ መስራች የክብር ዶክተር ዙምራ ኑሩም ይህንኑ ችግር በመገንዘብ ከአራት ዓመት እድሜው ጀምሮ ከሚያነሳቸው መሰረታዊ ሃሳቦች መካከል አንዱ " በጤና እጦትም ይሁን በእርጅና ምክንያት ተዳክመው ለስራ ብቁ ያልሆኑ አቅመ ደካሞችን መርዳት " የሚለው ይገኝበታል።
የክብር ዶክተር ዙምራ ኑሩም ሃሳቡን እንዲህ ሲል ይገልፃል " የወደቁ ደካሞች በጤናም ሆነ በእርጅና ምክንያት ከስራ ተፈናቅለው በየሜዳው ወድቀው ይበሉት ፣ ይጠጡት ፣ ይለብሱት ያጡ ሆነው አያለሁ ። ጠንካራው ከጠንካራው ጋር በልቶ ፣ ጠጥቶ ፣ ስቆ ፣ ተጫውቶ ሲወጣ አቅመ ደካሞችን የሚያስባቸው የለም ፥ እነዚህ ደካሞች እንደኛ ሰው ናቸው መብላት ፣ መጠጣት ፣ መልበስ ያስፈልጋቸዋል ያን እንዳያገኙ አቅሙ የላቸውም እኛ ጥለናቸው ከሄድን ማን ይደርስላቸዋል? እኛ ጥለናቸው ከሄድን እኛም አንድ ቀን እንወድቅ ይሆናል ። በምንወድቅ ጊዜ እሚያስበን እንፈልጋለን ። እኛ እሚያስበን እንደምንፈልግ ሁሉ ለምን እነሱን ጥለናቸው እንራመዳለን? ለሰው ደራሹ ሰው እንጂ ሌላ ማን ይመጣለታል? የሚል ጥያቄም ያነሳል።
አውራ አምባዎች ሰርቶ ሰርቶ ሲጨርስ የሚጣለው እቃ እንጂ የሰው ልጅ አይደለም ሲሉም ይደመጣሉ ። ከንግግር ባለፈም በተግባር እየኖሩት አሳይተዋል። በዚህ የአረጋዊያን ክፍል ውስጥ ደካማ ወገኖች የየራሳቸው የማረፊያ ክፍል ኖሯቸው ፣ በየሶስት ቀን የሰውነት ንፅህናቸው ተጠብቆ ፣ በየሳምንቱ ልብሳቸው እየታጠበ ፣ በየቀኑ የመኖሪያ ግቢያቸው እየተፀዳ በአረጋዊያን ተንከባካቢዎች ተገቢውን ምግብና እንክብካቤ እያገኙ በፍቅርና በደስታ እየኖሩ ይገኛሉ ።
የአውራ አምባ ማህበረሰብ "ትልቁ ሃብት ሰው ነው ፥ ሌላው ቀጥሎ የሚገኘው ገንዘብ ነው " ብሎም ያምናል ። ቀጥሎ የሚገኘው ገንዘብ ትልቁ ሃብት የሆነውን ሰውን ሰውን ለመመገብ የሚሆንና ተሰርቶ የሚገኝ ነው ይላሉ። ስለሆነም በእርጅናም ይሁን በጤና ችግር ምክንያት ሰርተው ራሳቸውን መደገፍ የማይችሉ ደካሞችን ዋስትናቸውን የሚሸፍነው ማህበረሰቡ ነው።
" ደካማ ወገንን መርዳት የእድገት መሰላል እንጂ ውድቀትን አያመጣም " የክብር ዶክተር ዙምራ ኑሩ ።
ሙሉ ቪዲዮውን ለመመልከት https://youtu.be/R31tnZGykgk
Click here to claim your Sponsored Listing.