MY PATH

MY  PATH

Share

03/04/2026

"ልጠይቅህ ሚስጢር "

በሠማይ በምድር የሞላህ እግዚሔር
አንዳችም በፊትህ ከቶ የማይሰወር
ኤልሻዳይ ነህና ልጠይቅህ ሚስጢር።
እንዴት ነው በሰማይ የገነቱ ስፍራ
ደግሞም የሲኦሉ ሠውን የሚያስፈራ
ቦታው አልጠገበም በዚህ ሁሉ ተጓዥ ሂያጁ በየተራ?
ነገሩን ባነሳም የተገረምኩበት
ሌላ ነው ጥያቄው የተጨነኩበት።
በዚች በምድራችን በምንኖርባት
ግፉ ሞልቶ ተርፎ በገነፈለበት
እልፍ አላአፍቱ በሚታጨዱባት
ግራና ቀኝ ያለዩ አበባ ህፃናት
በግፈኞች እብሪት ሲረግፉ በጥይት
ባዋቂ ተደፍረው ሲሞቱ በስቃይ
ይህን ሁሉ ክፋት እያየህ ከሠማይ
ግራ ስላጋባኝ የዝምታህ ነገር
አፌን በጄ ጭኜ ልጠይቅህ ሚስጢር።
ፃድቃን ከመሰዊው ሥር ለፍርድ ሲጠይቁህ
ቀሪው እስኪታረድ ጠብቁ እንዳልህ
ለዚህ ይሆን እንዴ የበዛው ዝምታህ
ኮታው እስኪሞላ የሚሞተው ህዝብህ
አይተህ እንዳላይ እንደህ ዝም ማለትህ?
በግፈኞቹ ላይ ያልነደደው ቁጣህ ?
ብለህ ይሆን እንዴ መምጫ ድልድይ ነው
በሞት ነው መንገዱ ወደኔ የሚመጣው ?

21/12/2025

" አብዮትና ሥነ- ሥርዓት "
(Gimini ርዕሱን ስለቀየረው እኔም ቀይሬዋለሁ)
በአገራችን የታዘብኩትን ከማንሳቴ በፊት ፣በቻይና አብዮታዊ የትጥቅ ትግል ወቅት፣ የተከሰተውን እንደ መንደርደሪያ ላንሳ።
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሠራዊቱን ከደቡባዊ ቻይና ወደ ሰሜን 1000 ማይል የእግር ጉዞ ያጓጉዝ ነበር። ይህን ታሪክ ፣ የአገሬ ተዋጊዎች፣ " THE RED STAR OVER CHINA " የተሰኘውን መፅሐፍ ፈልገው ለሚመሯቸው ተዋጊዎች ቢያስነብቧቸው ስለ ህዝባዊነትና ዲስፕሊን እንዲማሮ ስለ ሚጠቅማቸው መጠቆም እፈልጋለሁ።
ወደ ታሪኩ ቅንጫቢ ልመለስ።
የጉዞውን መራራና እልህ አስጨራሽ ፍልሚያውን በዐይነ ህሊናችሁ ተመልከቱልኝ። በጉዟቸው አንዲት ንግሥት የምታስተዳድረው ግዛት ደረሱ። አካባቢው በበግ እርባታ ይታወቃል። ማኦ ዜቱንግ ሠራዊቱን ሰብስቦ፣ በርሃብ እስከሞት ብትደርሱም የገበሬ በግ እንዳትነኩ፣ የአንድ በግ ህይወትና የአንድ አብዮታዊ ሠራዊት ዓባል ሂወት እኩል ይሆናል ፣አላቸው። ሠራዊቱ በርሃብ እየማቀቀና ሳርና ቅጠሉን እየተመገበ ጉዞውን ቀጠለ እንጂ አንድም የገበሬ ንብረት አልነካም ነበር። ማኦ ዜቱንግ እራሱ የሚያጨሰው ሲጋራ ስላጣ ፣ የደረቀ የዛፍ ቅጠል በወረቀት እየጠቀለለ ማጨስ ስለ ጀመረ ፣ ሠራዊቱ ድርጊመቱን በመቃወም በሠላማዊ ሰልፍ ተቃውሞ አስተውት።
ወደ አገራችን የ1983 ዓ.ም ትዝብቴ ልመልሳችሁ።
በወቅቱ ምዕራብ ሀረርጌ ፣ ጭሮ ከተማ እሠራ ነበር። ኢህአዴግ አገሪቱን የተቆጣጠረበት ጊዜ ነበር። መከረኛው አማራም በማንነቱ ይጨፈጨፍ ነበር ( የእንቁፍቱን ጭፍጨፋ ማስታወስ በቂ ይመስለኛል)። ከዚህ በፊት ፣ " አሚንን ልዘክረው" በሚለው ርዕስ ስር ወዳጀ አሚን በሚሰራበት መቻራ ከተማ ኦነጎችን ተጠግቶ በማማከር ግድያውን እንዲከላከል ለማድረግ እዚያው ድረስ ሄጀ ያደረግነውን ውጤታማ ተግባር በዚሁ ገፄ ላይ ለጥፌላችሁ ነበር። አሚንን፣ ለመሆኑ ወደ እዚች ከተማ የገቡት ምን ያህል የኦነግ ታጣቂዎች ናቸው፣ አልኩት። 38 ብቻ ነበሩ አለኝ። እነዚህ 38 ታጣቂዎች 3 ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቁኒ የተባለች ከተማ ላይ ብቻ 17,000 መድረሳቸውን ሰማሁ። የቁኔ ከተማ ከጭሮ ከተማ 20 ኪ.ሜ ብትርቅ ነው። በዚያው ሰሞን ይህ ሠራዊት የጭሮ ከተማን ሌሊት ሌሊት እየከበበ ከተማዋ ላይ መትረየሱን ሲያንበቀብቅብን ያድር ጀመር። መብራትና ውሃ አቋርጦብን ቤተሰቤ ከአንድ ወር በላይ ንፍሮ እየበላና የወንዝ ውሃ እየጠጣ ቆይቷል።
አንድ ቀን ሌሊት በጨለማ ከቁኒ ከተማ በኦነግ የተማረሩ ገበሬዎች ሹልክ ብለው ጭሮ መጡና ኢህአዲግን ከኦነጎች ነፃ አውጣን ብለው ከተማዋን በሠላማዊ ሠልፍ አጥለቀለቋት። ምን ሆናችሁ ነው ፣ብንላቸው፣ ኦነግ የጉድጓድ ማሽላችንን እያወጣ ሠራዊቱን ቀለበበት፣ ሰንጋ በሬዎቻችንን እያረዳ አበላቸው፣ ስንት ሺህ ብር እንሸጠዋለን ያልነውን የጫት ተክል ምርታችንን እየቆረጠ ሠራዊቲን አቃመብን፣ የቀፎአችንን ማር እየቆረጠ ማሩን አስበላብን፣ አሉን። እንቁላል፣ ዶሮ፣ እንጨት ፣ወዘተ ጭሮ ሄዳችሁ ለነፍጠኛ እንዳትሸጡ ተብለው በመከልከላቸው ምርታቸውን ሸጠው በሚያገኙት ገንዘብ፣ ጋዝ፣ ዘይት፣ ጨው፣ መድሃኒት፣ ወዘተ እንዳይገዙበት አደረጓቸው።
ኢህአዴግ ተንኮሉ፣ ሠላማዊ ሰልፍ ከተደረገ በኋላ ለሠልፈኞቹ ምላሽ ሳይሰጣቸው ዝሞ፣ ጭጭ፣ አላቸው። ገበሬዎቹ ወደ ቁኒ እንዳይመለሱ ፣ ሠላማዊ ሠልፍ በማድረጋቸው ኦነግ የሚበቀላቸው መሆኑን ስለ ፈሩ ወደ ቁኒ ከተማ ሳይመለሱ እዚያው ጭሮ ከተማ ረሃብ እየቆላቸው ከሳምንት በላይ ቆዩ። ኢህአዴግ እንዴት ጥቃት እንደሚፈፅም ሲያጠና ኖሯል አንድ ሳምንት የከረመው። የሀረር ገበሬ ከጧት ጀምሮ እስከማታ ጫቱን ሲቅም ነው የሚውለው ( ስለ ዚህ ጉዳይ ክቡር ግርማቸው ተክለሃዋሪያት፣ "አርዓያ " ብለው የፃፉትን መፅሐፍ ያነበበ ያቀዋል )። ታዲያ እነዚህን ገበሬዎች የሚቅሙት ጫት የምግብ ፍላጎታቸውን ስለ ሚዘጋቸው ቀን ብዙም አይመገቡም። እነሱን ረሃብ የሚለቅባቸው ሲነጋጋ ነው። ይህን ረሃብ ፣ "ጭንንቶ" ይሉታል፣ በግርድፉ ሲተረጎም ሆድን ሞረሙር ፣ ወይም ሆድን የሚናከስ ርሃብ ፣ እንደማለት ነው። ታዲያ እነዚህ የገበሬ ጦሮች ሲነጋጋ ከምሻጋቸው እየወጡ ምግብ ፍለጋ ወደ ከተማ እንደሚወርዱ፣ ኢህአዴግ ይደርስበታል። ከሳምንት በኋላ ሌሊቱን ከጭሮ ከተማ ጦሩ ተነስቶ በጫካ በኩል በእግር ተጉዞ ሲነጋጋ ቁኒ ተማ የሚገኘው የኦነግ ምሽግ ይደርሳል። ያን ጊዜ ገበሬዎቹ ምግብ ፍለጋ ከምሽጋቸው ወጥተው ምግብ ፍለጋ ወደ ከተማዋ ሄደዋል። በለቀቁት ምሽግ የኢህሀዴግ ታጣቂ እየገባ ምሽጉን ተቆጣጠረው። ኢህአዴጎቹ ልክ እንደ ኦነግ ታጣቂዎች ፀጉራቸውን አበጥረውና ሚዶም በጎፈሬቸው ራይ ሻጥ አድርገዋል። ሽርጥም አገልድመው ተመሳስለው ነበር። የኦነግ ታጣቂዎች ጭንንቷቸውን አስታግሠው ወደ ምሽጋቸው ሲመለሡ፣ አቦ አንተ ማነህ? እኔ ምሽግ ተሳስተህ ነው የገባኸው፣ አቦ ወደ ራስህ ምሽግ ሂድ እንጂ ፣ ይላሉ። በዚህ ጊዜ ኢህአዴግ በክላሽ ጥይት ደረት ደረታቸውን እያሉ 30 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በትንሽ ሜዳ ላይ ከበባ አድርገው ማረኳቸው። አሁን እኔ ይኸን ጀግንነት ነው ብየ ማውራት አደለም አላማየ። የኔ አላማ ለሠላማዊ ሠልፍ ጭሮ የሄዱት ገበሬዎች ከፈፀሙት በቀል የዛሬ ታጣቂዎች ትምህርት እንዲወስዱ ማሳሰብ ነው። ሠላማዊ ሠልፈኞች ኢህአዴጎቹን ከኋላ ኋላ ተከተለዋቸው ከጭሮ ከተማ መጥተው ነበር። እንዴት እነዚህን ትማርካላችሁ፣ እያሉ ፣በትንሽ ቦታ ላይ በተሰበሰቡት ምርኮኞች መሃል ቦምብ እየጣሉ፣ ኢህአዴግ ካደረሰው ጉዳት የበለጠ ግድያ ፈፀሙ። እነ ማኦ ዜቱንግ እና ሠላማዊ ሠልፈኞች ከፈፀሙት ድርጊት ያልተማረ ታጣቂ፣ ከወዲሁ ፣ዋ ! ለኔ፣ ብሎ ቢጠነቀቅ መልካም ነው እላለሁ። ያገሬ ሠው፣ " ማወቅ እንኳን እናውቃለን፣ ብንናገር ግን እናልቃለን፣ ብለን ነው እንጂ፣ ይላል በሥነ - ቃሉ። የተበደለ ህዝብ ቀን ያጋጠመው ቀን የበደለውን እንደሚበቀል አውቆ መጠንቅቅ ማትረፍ ነው። በ"ፍቅር እስከ መቃብር" መፅሐፍ እንደ ተገለፀው ከአበጀ በለው ተከታይ ገበሬ ከከወነው ተግባር እና ኮ/ል መንግሥቱኃይለማሪያም፣ በሰሜኑ ጦርነት፣ "ህዝቡ በሠራዊታችን ላይ እንደ አንበጣ ይሠፍርበታል፣" ብለው ከተናገሩት ኩነት መማር ብልህነት ነው።

Want your public figure to be the top-listed Public Figure in Dessie?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Telephone

Website

Address

Dessie