Amba 27
20/04/2025
የትንሣኤ ዋዜማ እርድ ስንት ሰዓት መታረድ እንዳለበት በሰጡት ማብራሪያ ግራ ተጋባን ላሉት ኦርቶዶክሳውያ
ክቡር ሊቀሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ ያስተላለፉት መልእክት።
👉🏻“መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም፤ ብንበላም ምንም አይተርፈንም ዳሩ ግን ይህ መብታችሁ ለደካሞች እንቅፋት እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ” 1ቆሮ. 8፥8 የመብልና የመጠጥ ጉዳይ በቤተ ክርስቲያን ከርክር ሁኖ ሊነሣ የሚገባው ዋና አጀንዳ አይደለም። ነገር ግን አይነሣ ነገር የለምና ከተነሣ ፍርዱ የሚሰጠው ምዕመናን እንዳይቸገሩ በሕገ ርኅራሄ የሚዳኝ ነው እንጅ እንደ ሌሎቹ ሃይማኖታዊ ክርክሮች ተጠየቅ ልጠይቅህ የሚል ሥርዓት የሚታይበት አይደለም። ጉዳዩ ሕዝብ እንዳይከፋፍል ተብሎ ካልሆነ ምድራዊ ሥርዓት ስለሆነ ነው። የእግዚአብሔር ሕግ ወንጌል ከሰማይ ስለወረደ እንጀራ የምንማርባት እንጅ ስለምድራዊ መብልና መጠጥ እያነሣን የምንከራከርባት መጽሐፍ ስላልሆነች ነው። ይህንንስ እግዚአብሔር አሳልፎታል፤ በሰማያዊ መና ተክቶታል።
በሰሞኑ ከፋሲካ በዓል እርድ ጋር ተያይዞ የተነሣው ትምህርት የተለያዩ መምህራን ሲይዙት የተለያየ መልስ እየተሰጠበት በመሆኑ ግራ የተጋባችሁ፣ ያዘናችሁ ምዕመናን እንዳላችሁ ከደረሱኝ መልዕክቶች ለመረዳት ችያለሁ። ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎችም ደስታቸውን ገልጸውልኛል። ዛሬ ይህንን መልዕክት ለመጻፍ የተነሣሁትም ለዚህ ነው። አስቀድሜ መግለጽ እምፈልገው በዚህ ጉዳይ ከማንም ጋር ሙግት እንደሌለኝ ነው። ከኔ ጋር የተስማሙትንም ሆነ ያልተስማሙትን ለመንቀፍም ለማመስገንም አይደለም።
እኔ ይህንን መልዕክት ሳስተላልፍ የተናገርሁበትን መንፈስ Intention ላስረዳችሁ። እኔ የተላክሁት ወንጌል እንድሰብክና ምዕመናንን ሁሉ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም እንዳቀርብ ነው። ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲወርሱ ከማድረግ በቀር ሌላ ዓላማ የለኝም። የሁሉም የቤተ ክርስቲያን መምህራን ተልዕኮም ይሄ ነው። የአንዲት ቤተ ክርስቲያን መምህራን እስከሆንን ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ ልዩነት ይኖርብናል ብየ አላምንም። ልዩነት የሚፈጠረው ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ጠርታ በምታገባው በወንጌል ትምህርታችን ሳይሆን በዚህ መካከል ዕንቅፋት የሚሆንባቸውን ነገር እያስወገዱ በመሄድ ጉዳይ ላይ ነው። የዛሬው አከራካሪ ጉዳይም ዕንቅፋትን የማስወገድ ጉዳይ ነው እንጅ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚያገባ መሠረታዊ የወንጌል ትምህርት የሚባል አይደለም።
እግዚአብሔር ፈቅዶ ከቀደመው ዘመን ይልቅ ይሄኛው ትውልድ ወደ ቅዱስ ቊርባን የሚቀርብ ትውልድ እየሆነልን ነው። ከአንድ ሰዓት ለሚበልጥ ጊዜ ካህናቱ ቆመው ሲያቆርቡ ስመለከት ነፍሴን ከዚህ በላይ የሚያስደስታት ነገር እንደሌለ ነው ምነግራችሁ። ነገር ግን የፋሲካ ዕለት ለመቊረብ ብዙ ሰዎች ሲቸገሩ ስላየሁ ነው በቪዲዮ ያያችሁትን ትምህርት የሰጠሁት። ከሥጋው ከደሙ የሚከለክለን ምንም አይነት ዕንቅፋት ሊኖርብን አይገባም። በዚያውም ላይ በጾም ደም ማፍሰስ ጾም ያስገድፋል ብሎ ማስተማርም ሃይማኖታችንን ግብዝ ያደርግብናል ሥጋ ባየን ቁጥር ጾም የምንሽር ከሆነ እንዴት ያለ ሃይማኖት ነው አያሰኝብንም? ሥጋ አትብሉ ነው እንጅ አትረዱ የሚልስ ሕግ አለ? ላንበላው ለምን እናርደዋለን? ካላልን በቀር። ደግሞስ ምዕመናን አማናዊውን ፋሲካቸውን ክርስቶስን በልተው ጠጥተው ደስታቸው ፍጹም እንዲሆንላቸው ልናበረታታቸው ሲገባ ማሰናከል አይሆንብንም? ቅዱሳን ሐዋርያት እንዳስተማሩን “ሕዝቡን እንዳናስቸግራቸው” ሥራ. 15፥19 አድርገን ማስተማር ይገባናል። ወጥተው ይረዱት እንዳንል ሥጋውን ደሙን ከተቀበሉ በኋላ ሊያከናውኑት የሚችሉት ነገር አይደለም፤ ይቅርባቸው እንዳንል በተዐቅቦ የሚኖር መነኩሴ ሳይቀር ሥጋ በልቶ ወይን ጠጥቶ ምስጋና በሚያቀርብበት ዕለት እንዴት ሥጋ ከመብላት እንከለክላቸዋለን? በዓመት ሁለት ጊዜ የልደትና የትንሣኤ በዋልድባና በማኅበረ ሥላሴ በሌሎችም ገዳማት በጽኑዕ ተጋድሎ የሚኖሩ መነኮሳትም ይህንን ቀን ሥጋ ይበላሉ ወይን ይቀምሳሉ። በምዕመናን ላይ እኛ የማንችለውን ቀንበር እየጫንን እንደሆነ ይሰማኛል።
አስቀድመን ወደ ቅዱስ ቊርባን ለመቅረብ የሚከለክላቸው ነገር እንዳይኖር እንጠንቀቅላቸው፤ ምዕመናንም ግራ አትጋቡ አትጨነቁ፤ መዳናችሁን ለመጠበቅ ይሕንን ምክንያት በማድረግ ከሥጋው ከደሙ እንዳትርቁ በቤተ ክርስቲያን ገብታችሁ “ትንሣኤከ ለዕለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ” ብላችሁ መዘመር እንዳይቀርባችሁ አጠናቃችሁ እንድትሄዱ ለማድረግ ነው። ከኔ የተለየ ሀሳብ ያላቸውም ሥርዐተ ጾም እንዳይሻር ብለው ነው። እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥማችሁ ለወደፊቱም መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ “ለደካሞች እንቅፋት እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ” እንዳለ እንደ ድካማችሁ አይታችሁ ዕንቅፋት የማይሆንባችሁን ትምህርት ምረጡ እንጅ ሁለቱም የተለያየ ሆኖባችሁ መሰቃየት የለባችሁም። ሥርዐት ለመሸርሸር ታስቦም አይደለም፤ ከሆነም ከመቊረብ የሚበልጥም የሚቀድምም ሥርዓት የለንም። ከዚህ የሚያርቀን ከሆነ ማንኛውንም ሥርዐት ማስተካከያ ልናደርግበት እንችላለን። በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ተሹመን ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን አናፈርስም።
አእምሯችሁን በሚያሳርፍ የእግዚአብሔር ሰላም ውስጥ ሆናችሁ የምታሳልፉትን የትንሣኤ በዓል በምንም ሁኔታ ልትረበሹ አይገባም የሚል ሀሳብ ስለተሰማኝ ይህንን መልዕክት ጻፍሁላችሁ።
ስምዐኮነ መላክ
ቪድዮውን ላልሰማችሁ ሊንኩን ተጭናችሁ አድምጡ
https://youtube.com/?si=kV_FJW4TX-8qZE3G
የትግስት ፍሬዋ
#ዘና
24/06/2024
Click here to claim your Sponsored Listing.