Method mode

Method mode

Share

Photos from Method mode's post 07/02/2026

“ያየን የለም እንጂ ያላየነው የለም”

ልጅ እያለን አንድ በሰፈራችን የታወቀ፥ ገዜ የተባለ ተወዛዋዥ ነበር፤ የሆነ ጊዜ ላይ የመቶ ሀያ ፕሮግራም አዘጋጆች ደብረማርቆስ መጥተው፥ ስለ ክልላችን የኪነጥበብ እንቅስቃሴ የሚዘግብ ፕሮግራም ሰሩ፤ በዚያ ፕሮግራም ውስጥ ። ገዜ ለአምስት ሰከንድ አካባቢ ወዝወዝ ሲል ይታያል ፤ ብልጭ ብሎ ይጠፋል ብንለው ይሻላል
ይቺም ዝና ሆና ፥ ገዜ ሊጠቀምባት ፈለገ፤ በማግስቱ፥ የከተማችን አንደኛ ቆንጆ ከገበያ ስትመለስ አስቁሞ ሊጀነጅናት ሞከረ፤ ፊትም ጀርባም ነሳችው፤
“አላወቅሽኝም ?”

“አላወቅሁህም” አለች ልጂቱ፤

ገዜ ቀብረር እያለ እንዲህ አለ፤

“ በሰፈራችሁ ቴሌቪዠን የለም መሰል “

ለመጀመርያ ጊዜ ቴሌቭዠን የገዛሁበትን ሁኔታ አልረሳም፤ አልበላም አልጠጣም አለብስም ብየ፥ የሸመትሁት ባለ ሃያ አንድ ኢንቺ ቲቪ፥ ካዲስ አበባ ወደ ደብረማርቆስ ሲጫን እንዳይሰበር፥ እንደ እንቁላል በጭድ በተሞላ ካርቶን ውስጥ ተመስጎ ነበር ፤

የከተማው ህዝብ አሳዩን እያለ እንዳያስቸግረን ሰግተን ፥ እንደ ተጠለፈች የገጠር ሙሽራ በጠፍ ጨረቃ ይዘነው ገባን፤ ወንድሞቼና እህቶቼ ቲቪው ላይ በታላቅ ተመስጥኦ ተጣዱበት ፤ ፓርላማ አይቀራቸው፤ ዜና አይመክታቸው ሜትሮሎጂ አያልፋቸው ፤

አብርያቸው ስመለከት አመሸሁና እንቅልፍ ክንብል አረገኝ ፤ እኩለሌሊት ላይ የቲቪ ፕሮግራሙ አልቆ ስክሪኑ ሽሽሽሽ በሚልበት ሰአት, ሞሴ የተባለው የመጨረሻው ታናሽ ወንድሜ ትከሻየን አርገፍግፎ ቀሰቀሰኝ፤
“ምን ፈለግህ?” ስለው፥

“ ቴሌቭዡኑ ተሰናክሏል ፤ ተነስተህ ጠግንልን “🙂

አሁን እያንዳንዱ ሰው መዳፉ ላይ ስክሪን አለ፤ የቱን አይተን የቱን እንደምንተው ግራ ገብቶናል፤ የድሮ ሰው ጥሞና ነበረው፤ ቪክቶር ሂጎ የተባለ ደራሲ አንድ ስእል ለማጣጣም አንድ ቀን ፈጅቶበታል ይባላል፤ አሁን ሁሉም ሰው በየቤቱ የሚታይ ነገር ያመርታል፤ ማን ታይቶ ማን ይቀራል?

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የሳንቲም ተመጽዋች ብቻ ነበር ያለው፤ አሁን የትኩረት ተመጽዋችም ተፈጥሯል ፤ “በፈጠራችሁ ይህንን ቪድዮ እንዳታሳልፉት “ ብሎ አንጀት በሚበላ ድምጽ የሚማጸን ማየት ተለመደ;

መኖር አይንን ለማስገበር የሚደረግ ግብግብ ሆኗል፤ መሰርያው በያይነቱ ይወለወላል፤ እንግዳ አለባበስ፥ ወጣ ያለ መፈክር፥ ብዙ ጥቅም ላይ ያልዋለ ጠገራ ስድብ ታጥቀው እሚሰለፉ አሉ፤ በተቃራኒ የስነምግባር ወኪል፤ የትውልድ ተቆርቋሪ ፥ የባህል በረኛ ሆነው የሚጫወቱም አይጠፉም፤

ለጊዜው ከሁለቱም ወገን ያልሆንነው፥ ተርታችን እስኪደርስ ፥ “ ያየን የለም እንጂ ያላየነው የለም” በሚለው የጠቢቡ ወያላ ጥቅስ ተጽናንተን ፤ ከፈንድሻው ቃም ቃም እያረግን ግብግቡን በተመስጦ እንከታተላለን::

https://t.me/matter_of_facts

Want your business to be the top-listed Photography Service in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Category

Telephone

Website

Address

Renowned
Addis Ababa