Daamileen Lafa

Daamileen Lafa

Share

09/10/2025

Fkn...Falmattuu mirga dhal-namummaa

09/05/2025

መለስ ዜናዊን በጨረፍታ (ክፍል አንድ)
----
ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ
---
በኢትዮጵያ ታሪክ ለረጅም ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት አቶ መለስ ዜናዊ የተወለዱት ግንቦት 1/1947 በትግራይ ክልል በአድዋ ከተማ ነው፡፡ መለስ የልደት ስማቸው “ለገሠ ዜናዊ” ነበር፡፡ ተማሪ ለገሠ ዜናዊ በትምህርቱ በጣም ጎበዝ እንደነበረ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነው። እስከ ስምንተኛ ክፍል የተማረው በአድዋው ንግሥተ ሳባ ትምህርት ቤት ሲሆን የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ (Highschool) ትምህርቱን ደግሞ በጄኔራል ዊንጌት ሁለተኛ ትምህርት ቤት ነው ያጠናቀቀው።

ለገሠ ዜናዊ በ1966 ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ በህክምና ፉኩልቲ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ህክምናን አጥንቷል። የፖለቲካ ተሳትፎውንም የጀመረው በዩኒቨርሲቲው የሚማሩ እና በመንግሥት ስራ የተሰማሩ የትግራይ ተወላጆች በህቡዕ የመሠረቱት "ማኅበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ" (የትግራይ ብሄር ተራማጆች ማኅበር) አባል በመሆን ነው። የዚሁ ህቡዕ ማኅበር አባል የነበሩ የትግራይ ተወላጆች በየካቲት 1967 ወደ ደደቢት በረሃ ወርደው የትጥቅ ትግል መጀመራቸው ሲሰማ ተማሪ ለገሠ ዜናዊ በሚያዚያ ወር 1967 ትምህርቱን አቋርጦ ወደ በረሃ ወርዷል።
-----
እንግዲህ የያኔው ተማሪ ለገሠ ዜናዊ “መለስ” በሚለው ስም መጠራት የጀመሩት ለትግል ወደ ደደቢት በረሃ ከገቡ በኋላ ነው፡፡ በወቅቱ እርሳቸው በተቀላቀሉት ተሓሕት (ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ) ደንብ መሰረት ለቤተሰብ ደህንነት ሲባል ስምን መቀየር የተለመደ ስለነበረ ነው መለስም ስማቸውን የቀየሩት፡፡ “መለስ” የሚለው ስም በ1967 መጋቢት ወር “ከኤርትራው ጀብሃ ወንበዴዎች ጋር ተባብረህ የአዲስ አበባን ማዘጋጃ ቤት በፈንጂ አጋይተሃል” ተብሎ ከተረሸነው “መለስ ተኽለ” ከተባለው ወጣት ስም የተወሰደ ነው፡፡ እዚህ ገደማ ግን አንድ ነገር ልብ ሊባል ይገባል፡፡

እነ መለስ ዜናዊ የመሰረቱት “ተሓሕት” ለትግራይ ህዝብ በመፋለም ረገድ የመጀመሪያው ድርጅት አይደለም፡፡ ከዚህ ድርጅት በፊት በ1966 መገባደጃ ላይ “ግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ” (ግገሓት) የተባለ ድርጅት በትግራይ ተራማጅ ወጣቶች ተመስርቶ ነበር፡፡ ይህ ድርጅት በአብዛኛው በኤርትራው “ጀብሃ” የሚደገፍ ሲሆን እስከ የካቲት 1967 ድረስ በትግራይ ገጠር አካባቢዎች አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን አካሂዶ ነበር፡፡ እንደዚሁም ጀብሃ በአዲስ አበባ ባካሄዳቸው የቦምብ ፍንዳታዎች ተሳትፎ እንደነበረው ይነገራል፡፡

በየካቲት 11/1967 የተመሰረተው ተሓሕት ከእርሱ በፊት ከተመሠረተው ግገሓት ጋር ለመዋሀድ ጥያቄ አቅርቦ ነበር ይባላል፡፡ ይሁንና ሁለቱ ድርጅቶች ሊስማሙ አልቻሉም፡፡ በሁለቱ መካከል ለተከሰተው ፍጥጫ ትክክለኛው ምክንያት ምን እንደነበረ መገመት ያስቸግራል፡፡ የተሓሕት አባላት የነበሩት ግገሓት ገበሬውን በማስጨነቅና የሀገሬውን ህዝብ አስገድዶ በመዝረፍ የሽፍታ እንቅስቃሴ ተሳታፊ በመሆኑ ተሓሕት እርምጃ ለመውሰድ እንደተገደደ ይናገራሉ፡፡ ከግገሓት ጋር ቅርበት የነበራቸው ምንጮች ግን "ተሓሕት የትግራይ መሬት ከአንድ ድርጅት በላይ የመሸከም አቅም የለውም" በሚል መሰሪ ዓላማ ተነሳስቶ ድርጅታቸውን እንዳጠፋው ነው የሚገልጹት፡፡ ከሁለቱም ወገን ያልነበሩ ወገኖች ደግሞ ድርጅቶቹ እስከ መጠፋፋት የደረሱት ሻዕቢያ እና ጀብሃ ከጀርባቸው ስለነበሩ ነው ይላሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ ግገሓት በትግራይ ምድር ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ መቆየት አልቻለም፡፡ እርሱ ሲጠፋ የትግል ሜዳው ለተሓሕት አመቺ ሆኖለት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡
------
መለስ ዜናዊ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በድርጅቱ አመራር ውስጥ አልነበረም፡፡ ከርሱ ይልቅ ድርጅቱን ይመሩ የነበሩት እነ አረጋዊ በርሀ (በሪሁ)፣ ፋንታሁን ዘርዓ ጽዮን (ግደይ)፣ መሓሪ ተኽለ (ሙሴ )፣ ዘርዑ ገሠሠ (አግዓዚ)፣ አታኽልቲ ጸሐየ (ኣባይ)፣ እምባዬ መስፍን (ስዩም) እና ወልደሥላሴ ነጋ (ስብሓት) ነበሩ፡፡ የመለስ ዜናዊ ፖለቲካዊ ስብዕና ጎላ ብሎ መታየት የጀመረው በ1969 በድርጅቱ ላይ የመበተን አደጋ በተጋረጠበት (በድርጅቱ ታሪክ “ሕንፍሽፍሽ” ተብሎ በሚጠራው) አስቸጋሪ ወቅት በተለይም የገለልተኝነት ስሜት ከነበራቸው ወጣቶች ጋር በማበር ድርጅቱን ለማትረፍ ብዙ በመልፋታቸው ነው ይባላል፡፡

በወቅቱ መለስ በፖለቲካ ስራዎች ላይ የተመደቡ ኮሚሳር ነው የነበሩት፡፡ አንዳንድ የሕንፍሽፍሽ ንቅናቄ መሪዎች “መለስ ዜናዊ አንድ ውጊያ በማበላሸቱ የሞት ፍርድ ሊፈረድበት ይገባል” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ቢጽፉም ይህንን ጉዳይ ከነጻ ወገን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ብዙሃኑ ጸሐፊያን መለስ በወቅቱ ገለልተኛ ነበረ በሚለው ይስማማሉ፡፡
----
በ1971 ድርጅቱ ስያሜውን “ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ” (ሕወሓት) ብሎ ሲቀይር መለስ ዜናዊ የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኑ፡፡ በዚህ ወቅት መለስ የድርጅቱ የፖለቲካ ትምህርት ቤት ኃላፊ በመሆን የካድሬዎችና የፖለቲካ ኮሚሳሮችን ስልጠና በበላይነት ይመሩ ነበር፡፡ ለአቶ መለስ ዜናዊ ይህ ጊዜያቸው ወርቃማ ዘመናቸው ነበረ ለማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ይህ ወቅት ለስልጠና የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎችን ለማዘጋጀት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከፕራግማቲክ ታጋይነት ወደ ጥልቅ አንባቢነት የተለወጡበት ጊዜ ስለሆነ ነው፡፡ ይህ ከንባብ ጋር ያዳበሩት ቁርኝታቸው ውጤቱ በ1977 በተካሄደው የድርጅቱ ጉባኤ እና የማሌሊት ንቅናቄ ወቅት በግልጽ ወጥቷል፡፡ በነገራችን ላይ መለስ ዜናዊ ከባለቤታቸው ከአዜብ መስፍን ጋር በፍቅር የወደቁት በዚህ ወቅት ነበር፡፡ ሆኖም በድርጅቱ ደንብ መሰረት በወቅቱ ጋብቻ ቀርቶ የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ እንኳ ለከባድ ቅጣት የሚዳርግ በመሆኑ መለስ አዜብን ለማግባት ስድስት ዓመታትን መጠበቅ ነበረባቸው፡፡
----
እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1977

መለስ ዜናዊ እጅግ ከፍተኛ እመርታ በማሳየት የድርጅቱ የወደፊት ዐይን መሆናቸውን ያስመሰከሩበት ዓመት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት በድርጅቱ ውስጥ ኮሚኒዝምን በሰፊው ማስረጽ ይገባል በሚል እሳቤ አንድ የፓርቲ አስኳል ተመስርቶ ነበር፡፡ ይህም “ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ” (ማሌሊት) የሚባለው ሲሆን የዚህ እንቅስቃሴ መሪዎች ኣባይ ጸሐየ እና መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ ይህ ፓርቲ “ኮሚኒስታዊ ርዕዮት በትክክለኛ መልኩ ወደ ታጋዩ እና ወደ ህዝቡ ካልሰረጸ ትግላችን ውጤታማ አይሆንም፤ ውጤታማ ቢሆን እንኳ አብዮታችን ሊቀለበስ ይችላል የሚል” እይታ ነበረው፡፡ ድርጅቱ በወቅቱ ኮሚኒስታዊ በመሆኑ እነ መለስ ታጋዩን ለማሳመን ብዙም አልቸገራቸውም፡፡ ነገር ግን “እነ መለስ የሚሉት ነገር ጽንሰ ሃሳባዊ እንጂ ፕራግማቲክ አይደለም፤ በተጨባጭ ለመተግበር የማይቻል ጽንሰ- ሃሳብ እያመጣን ታጋዩን ማወዛገቡ ይቅርብን” የሚል ተቃውሞም ተነስቶ ነበር፡፡ የዚህ ተቃውሞ መሪዎችም አረጋዊ በርሀ እና ግደይ ዘርዓ ጽዮን ነበሩ፡፡

ሁለቱ እይታዎች በየፊናቸው ድጋፍ ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ በወቅቱ የገለልተኝነት አቋም ያሳዩ የድርጅቱ አመራሮች “ነገሩ ሌላ ውዝግብ ከማምጣቱ በፊት በጉባኤ ይለይለት” የሚል የመፍትሔ ሃሳብ አቀረቡ፡፡ በዚህ መሰረት መለስ ዜናዊ የማሌሊትን አቋም፣ በመወከል ግደይ ዘርዓ ጽዮን ደግሞ የአፍቃሬ-ፕራግማቲክ ጎራውን በመወከል በ600 ጉባኤተኞች ፊት እንዲከራከሩ ተጋበዙ፡፡ (በወቅቱ ክርክሩን በዳኝነት የመሩት አርከበ ዕቁባይ ነበሩ)፡፡

መለስ ዜናዊ እና ግደይ ዘርዓ ጽዮን ለሁለት ሰዓታት ያህል የጦፈ ክርክር አደረጉ፡፡ በመጨረሻ ግን አንደበተ ርቱእ የሆኑት መለስ ዜናዊ ጉባኤተኛውን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ቻሉ፡፡ በተለይም ግደይ ዘርዓ ጽዮን “በቀኝ በኩል ካፒታሊዝምንና ኢምፔሪያሊዝምን፤ በግራ በኩል የሶቪየት ከላሽነትን የምትዋጋና የራሷን ሉዓላዊነት በማስከበር ሶሻሊዝምን መገንባት የቻለች አንዲት ሀገር በምሳሌነት ማቅረብ ትችላለህ?” በማለት ላቀረቡት ጥያቄ አቶ መለስ ዜናዊ “እንዴታ! አልባኒያ ጥሩ ምሳሌ ትሆናለች” የሚል ቅጽበታዊ መልስ መስጠታቸው ጉባኤተኛውን በረጅሙ አስጨብጭቦት እንደነበረ ታሪኩን የሚያውቁ ሰዎች በተደጋጋሚ የጻፉት ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ ጉባኤ በኋላ ግደይ ዘርዓ ጽዮን እና አረጋዊ በርሀ በድርጅቱ ውስጥ ብዙም አልቆዩም፡፡ መለስ ዜናዊ ግን የድርጅቱ የፖሊት ቢሮ አባል ሆኖ የተመረጠው በዚህ ጊዜ ነው፡፡
----
(ይቀጥላል)
-------
ግንቦት 1/2007
በሀረር ከተማ ተጻፈ።
-----
ትክክለኛዎቹ የሶሻል ሚዲያ አድራሻዎቼ የሚከተሉት ናቸው።

= የፌስቡክ ፔጅ (My New page)

https://www.facebook.com/AfendiEthno2018

=> የቴሌግራም ቻነል (My Telegram Channel)

https://t.me/afandishaHarar

Want your public figure to be the top-listed Public Figure in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Category

Address

Addis Ababa