Ethio-Lab Page

Ethio-Lab Page

Share

A wealth of discovery built on the Human Genome Project — by the numbers 13/02/2021

የሰው ልጅ የዘረ-መል ጥናት ፕሮጀክት
===================

የመጀመሪያውና ታላቁ የሳይንስ ምርመር የተባለው የሰውን ዘረ-መል የመደርደር ስራ ነበር፡፡ ይህም በ1990 (እ.ኤ.አ) ተጀመሮ በ2001 የመጀመሪያው ድራፍት ተጠናቋል፡፡ 2021 20ኛ የጉዞ አመታትን የገመገመው ኔቸር-መጽሔት ጠቅለል ያለ መረጃ ይዞ ወጥቷል፡፡
በዚህ በ20 ዓመታት ጉዞው የሰው ልጅ ካሉት ከ30,000 በላይ የሚሆኑ በራሄዎች ውስጥ በስፋት የተጠኑትና የታወቁት ከ8 አይበልጡም፡፡ እስከ 2017 ባለው ጊዜ የተሰሩ ስራዎችን በምንመለከትበት ሰዓት 22 ፐርሰንት የሚሆኑት የዘረ-መል ጥናቶች ያተኮሩት 1ፐርሰንት በሚሆኑት በራሄዎች ላይ ነው፡፡ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከታወቁት ውስጥ TP53 (9232 ምርምሮች ታትመውበታል), TNF, EGFR፣ TL6, VEGFA, APOE, TGFB1… የሚባሉት በራሄዎች ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

ሲጠቃለል በርካታ ስራዎች ቢሰሩም፣ ሳይንስ የሰው ልጅ የዘረ-መል ስሪትን ለማወቅ የጀመረው ጉዞ ገና በጭልፋ የመቅመስ ያክል እንጅ ምንም የታወቀ ነገር የለም፡፡

የሰው ልጅ ከባህርም ከውቅያኖስም፣ ከህዋም በላይ የማይታወቅ አስገራሚ ፍጥረት ነው፡፡ ክብር ሰውን ለፈጠረ ፈጣሪ

A wealth of discovery built on the Human Genome Project — by the numbers A new analysis traces the story of the draft genome’s impact on genomics since 2001, linking its effects on publications, drug approvals and understanding of disease.

23/01/2021

የኮቪድ-19 አንቲቦዲ መመርመሪያ መሳሪያዎች ጥራትና ብቃት፡ የምርምሮች ጭምቅ ውጤትና ትንተና
============================

በ2019 (እ.ኤ.አ) የተነሳውና ሳርስ ኮሮና ቫይረስ-2 በመባል የሚታወቀው ወረርሽኝ፤ ኮቪድ-19 የተባለ ደረቅ የሳንባ ምች በሽታ በማምጣት የአለም ፈተና እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ኮሮናቫ ይረስ በሚለው ዝርያ ውስጥ 7 ዓይነት የሰው በሽታ አምጭ ኮሮና ቫይረሶች የሚታወቁ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አዲሱ ሳርስ ኮሮና ቫይረስ-2 ከሁሉም ኮሮና ቫይረሶች በከፋ መልኩ በጣም ተላላፊ ቫይረስ ነው፡፡ በጆንሆፕኪንስ ዩንቨርሲቲ የበይነ መረብ መረጃ ቋት መሰረት 98 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው ሲታመሙ፣ 2.1 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት የአለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ትስስር ባህሪዎች እየተቀየሩ ናቸው፡፡
---
በእያንዳንዱ ሰው ቫይረሱ መኖር አለመኖሩን ምርመራ ለማድረግ አለም እየተጠቀመበት ያለው የላቦራቶሪ መሳሪያ የቫይረሱን ዘረ-መል መሰረት ያደረገ RT-PCR የሚባል መሳሪያ ነው፡፡ ይህ መሳሪያ በአለም የጤና ድርጅት እውቅና የተሰጠውና የአለም የጤና ድርጅት በሚያስተዳድራቸው ሀገራት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝ መሳሪያ ቢሆንም፤ በርካታ ጉድለቶች አሉበት፡፡ ከጉድለቶቹ መካከል የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
1. ከጉሮሮ ወይንም አፍንጫ ውስጥ የሚወጡ ፈሳሾችንን የሚጠቀም ስለሆነ በናሙና አወሳሰድ ላይ ስህተት ከተፈጠረ ውጤቱ ትክክለኛ ላይሆን ይችላል፡፡ በተለይ ቫይረሱ እያለ የለም የማለት ባህሪ ያሳያል፡፡
2. መሳሪያው ውድና በቂ ክህሎት ባላቸው የላቦራቶሪ ባለሙያዎች ብቻ የሚሰራ መሆኑ፣ በሁሉም ቦታ ተደራሽ ለማድረግ አስቸግሯል፡፡
3. መሳሪያው በየጊዜው የጥራት ሁኔታው መፈተሽ አለበት፣ ለዚህ ተብሎ የሚዘጋጀው ኬሚካል ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ እጥረት ይታይበታል፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ ጥራቱን ጠብቆና አገልግሎቱ ሳይቆራረጥ ለመስራት ትልቅ ተግዳሮት ነው
4. ቫይረሱ ዘረ-መሉን ሊቀይርና ከመመርመሪያው መሳሪያ እይታ ውጭ በመሆን የተሳሳተ ውጤት ሊያወጣ ይችላል፡፡
5. ከዚህ በተጫመሪ ምርመራው በራሱ አድካሚና ቀናትን የሚወስድ ነው፡፡
ስለሆነም በ15 እና በ30 ደቂቃ ውስጥ ውጤት የሚሰጡ፣ በትንሽ ስልጠኛ ከላቦራቶሪ ባለሙያዎች ውጭ ያሉ ሰዎች ጭምር ሊጠቀሙበት የሚችል፣ የጥራት ደረጃቸው አስተማማኝ የሆነ፣ ከጉሮሮና አፍንጫ ሳይሆን በደም ናሙሳ መስራት የሚችሉ፣ በሽታው የቅርብ ጊዜና የሩቅ መሆኑን መለየት የሚችሉ፤ ፈጣን የመመርመሪያ መሳሪያዎች መስራትና ገበያ ላይ ማዋል የአለም የመጀመሪያውና ከፍተኛው ፍላጎት ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ፍላጎቶች ሊያሟሉ የሚችሉ መሳሪዎችን ለማምረት በርካታ ኩባንያዎችና የዩንቨርሲቲ የምርምር ላቦራቶሪዎች በሽቅድድም ላይ ነበሩ አሁንም ናቸው፡፡ በመሆኑም ወረርሽኙ በገባ በወራት ውስጥ በርካታ ኩባንያዎች ጥራት ያለው ፈጣን መመርመሪያ መሳሪያ/ኪት/ ሰርተናል በማለት ምርታቸውን በተለያዩ ሀገራት እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡ የጥራት ተቆጣጣሪ ጅርቶችና የአለም የጤና ድርጅትም እውቅና እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
በመሆኑም እነዚህን እንደ አሸን የፈሉ የመመሪመሪያ መሳሪያዎች የጥራት ደረጃቸውን መፈተሽ፣ አንድም መርጦ ለመጠቀም በሌላ መልኩ የጥራት ጉድለት ያለባቸው መሳሪያዎች ገበያዉን ሰብረው በመግባት ፈቃድ እንዳያገኙና የጤና ስርዓቱን እንዳይጎዱት ሳይንሳዊ ፍተሻና ቁጥጥር ማደረግ ያስፈልጋል፡፡
---
የእኛ የምርምር ቡድን፣ በአለም ላይ በተለያዩ ካምፓኒዎችና የምርምር ተቋማት የተሰሩትን የኮቪድ-19 ፈጣን መመርመሪያ መሳሪያዎች ላይ የጥራት ፍተሻ ያደረጉ ምርምሮችን ወደ አንድ በማምጣት ጭምቅና ድምር ውጤታቸው ምን እንደሚመስል ማየት ነው፡፡ የተሰሩት ፈጣን የመመርመሪያ መሳሪያዎች ጥራት የተፈተሸዉ ደግሞ በመሳሪያዎቹ አይነት፣ የተጠቀሙትን የአንቲጅን አይነትና የአንቲቦዲውን አይነት ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
------------------------
ውጤት
----------------------
በ8 ሀገራት የሚገኙ የ47 ካምፓኒዎችን ፈጣን መመርመሪያ መሳሪያዎች የጥራት ሁኔታ የሚገልፅ መረጃ የያዙ 24 የምርምር ስራዎች ማገኘት ችለናል፡፡ የመመርመሪያ መሳሪያዎቹ በሶስት ዋና ዋና አይነቶች የሚመደቡ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ እነሱም በኢንዛይም የሚሰራ ኢላይዛ (Enyme-linked immunosorbent assay)፣ በኬሚካል የሚሰራ ኢላይዛ መሳይ መመርመሪያ( Chemiluminescence immunoassay) እና አር-ዲ-ቲ (Colloidal-gold lateral-flow immunoassays) ናቸው፡፡
ከሶስቱ መካከል በኬሚካል የሚሰሩት የመመርመሪያ አይነቶች የተሻሉ የጥራት ደረጃ ያላቸው ሆነው ተግኝተዋል፡፡ ለምሳሌ በRT-PCR ፖዘቲቭ የሆኑ 100 የኮቪድ-19 በሽተኞች በአዲሱ መሳሪያ ሲሰራላቸው በአማካይ 92% (95% CI: 86-95%)ቱን ፖዘቲቭ ሲል 8 ሰዎችን በስህተት የለባቸውም/ኔጌቲቭ ናቸው የማለት ባህሪ አሳይቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በRT-PCR ተመርምረው የለባችሁም የተባሉትን 100 ሰዎች በዚሁ በአዲሱ መመርመሪያ ሲመረመሩ 99% (CI: 97-99%) ኔጌቲቭ ብሎ አንድን ሰው ግን በስህተት ኮቪድ-19 አለበት የማለት ባህሪ አሳይቷል፡፡ ስለሆነም የዚህ መሳሪያ sensitivity 92% (95% CI: 86-95%) ሲሆን specificity 99% (CI: 97-99%) ሆኗል (የሮክ ከርቭን ምስል ይመልከቱ)፡፡
በተመሳሳይ አገላለፅ በኢንዛይም የሚሰራው የኮቪድ-19 ኢላይዛ በሽታው አለ የማለት አቅሙ (sensitivity) 86% (CI: 82-89%) ሲሆን specificity ደግሞ 99% (CI: 98-100%) ነው፡፡ የአር-ዲ-ቲዎች ጭምቅ sensitivity 78% (CI: 71-83%) ሲሆን specificity 98% (95%CI: 96-99%) ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ከበርካታ የአንቲጅን አይነቶች መካከል RBD የተባለውን አንቲጅን የተጠቀሙ መሳሪያዎች የጥራት ደረጃቸውን በተወሰነ መልኩ ከፍ አድርጎት ይታያል፡፡ ከሶስቱ የአንቲቦዲ አይነቶች (IgA፣ IgM እና IgG) መካከል 3ቱን መሰረት አድርገው ለመመርመር የተሰሩት መሳሪያዎች የጥራት ደረጃቸው በተወሰነ መልኩ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተናጠል በምናይበት ሰዓት IgA መኖሩን ለማረጋገጥ የተሰሩት አንፃራዊ የተሻለ ጥራት እንዳላቸው ያሳያል፡፡ ነገር ግን ይህን አንቲቦድ መሰረት አድርገው የተሰሩት መሳሪያዎች ትንሽ በመሆናቸው፤ በትንሽ መረጃ ተነስተን የተሻለ ነው ለማለት ብዙ አያስደፍርምና ወደ ፊት ቢታሰብበት የሚል ምክር እንሰጣለን፡፡ IgM ወይንም IgG እንዲሁም ሁለቱን በተጠቀሙ መሳሪያዎች መካከል የሰፋ የጥራት ልዩነት አልታየም፡፡
ሲጠቃለል በኬሚካል የሚሰራው መመርመያ የተሻለ ሲሆን የኮቪድ-19 የአር-ዲ-ቲ መመርመሪያ አይነቶች ግን ከፍተኛ የሆነ የጥራት ችግር ያለባቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ይህ መረጃ ለአለም የጤና ድርጅት ቀድሞ የተሰጠ ሲሆን ድርጅቱ ከሁሉም አለም ባሰባሰበው መረጃ መሰረት በስሩ የሚያስተዳድራቸውን የድሃ ሀገራት የጤና ስርኣትን አቅጣጫ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በራሳቸው መረጃና ኢኮኖሚ የሀገራቸውን የጤና ስርዓት የሚመሩ ሀገራት ግን እነዚህን መሳሪዎች እንደየ አስፈላጊነቱ ሊጠቀሙባቸው ይችላል፡፡
ይቆየን

Methicillin-resistant Staphylococcus aureus with genotyping method among human immunodeficiency virus positive pediatric patients in Northwest Ethiopia: A cross-sectional study design | Ethiopian Journal of Health Development 12/01/2021

የሜቲሲሊንን መድሃኒት የተላመደ የስታፊሎኮከስ አወረስ ባክቴሪያ ስርጭት፡ ከኤች.አይ.ቪ ጋር ከሚኖሩ ህፃናት ላይ
Methicillin-resistant staphylococcus aureus among HIV positive Children
========================================

በአሁኑ ሰዓት በአለም ላይ ሜቲሲሊን የሚባለውን የመድሃኒት ዓይነት የተላመደ ስታፊሎኮከስ አወረስ የሚባለው የባክተሪያ አይነት መጠኑ እየጨመረና ለአለም አሳሳቢ እየሆነ እንደመጣ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ በተለይም በኤች. አይ. ቪ የተያዙ ሰዎች ላይ ችግሩ ጎልቶ ይታያል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ የችግሩ መጠን ምን ያህል እንደሆነ የሚያመላክት በቂ ጥናት አልነበረምና ይህንን ጥናት ለማካሄድ መነሻ ሆኖናል፡፡
-
የጥናቱ መረጃ የተሰበሰበው ከታህሳስ-የካቲት 2006 ዓ.ም ባለው ወቅት ሲሆን ጥናቱ የተካሄደውም በአማራ ክልል ውስጥ ባሉ በተመረጡ የኤች አይ-ቪ ክሊኒኮች ነው፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑና የኤች አይ-ቪ/አድስ ክትትል በሚያደርጉ ህፃናት ላይ ሆኖ ናሙና የተወሰደው ከአፍንጫ፤ ፊንጢጣና እጅ ላይ ነበር፡፡ ከ3ቱ ቦታዎች ናሙና ከተሰበሰበ በኋላ ካልቸር ሚድያ ላይ ተዘርቶ በ35 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ የሙቀት መጠን ውስጥ ለ18 ሰዓታት ተቀምጧል፡፡ ከዚያ በኋላ ያደጉት ባክቴሪዎች እነማን ናቸው የሚለውን ለማወቅ የተለያዩ የመለያ ዘዴወችን ተጠቅመናል፡፡ በተለይ ስታፊሎኮከስ አወረስን ከሌሎች ለመለየት ልዩ የማሳደጊያ ሚዲያዎችን ተጠቅመናል፡፡ስታፊሎኮከስ አውሬስ ከተለየ በኋላ ከዚህ ባክቴሪያ መካከል የምን ያህሉ ሰው ሜቲሲሊን የተባለዉን መድሃኒት የተላመዱ ናቸው የሚለዉን ለማወቅ “Genotype MRSA VER 3.0” የተባለ ዘረ-መልን መሰረት አድርጎ ለምርመራና ምርምር የሚውል ኪት ተጠቅመናል፡፡
--
በዚህ ጥናት መሰረት ናሙና ከተወሰደላቸዉ 400 ህፃናት መካከል 126ቱ ስታፊሎኮከስ አወረስ የተባለዉ ባክተሪያ የተገኘባቸዉ ሲሆን፡ ከ126ቱ መካከልም 47 (37.3%) የሚሆኑት ሜቲሲሊን የተባለውን መድሃኒት የተላመደ ባክቴሪያ የተሸከሙ ሆነዉ ተገንተዋል፡፡ ከእነዚህ 47 ህፃናት መካከል ደግሞ 32ቱ ይህን መድሃኒት የተላመደ ባክቴሪያ የተቀበሉት ሆስፒታል ሲመላለሱ (ሆስፒታል ወለድ) ሲሆን ቀሪዎቹ 15 በሰፈር ውስጥ ከህብረተሰቡ ጋር በሚያደርጉት መስተጋብሮች ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለዚህ፣ አብዛሃኛዎቹ ህፃናት ለዚህ መድሃኒት የተላመደ ባክቴሪያ የተጋለጡት ለህክምና ክትትል ወደ ጤና ተቋማት ሲሄዱ ጤና ተቋም ውስጥ ነው የሚል ድምዳሜ ደርስናል፡፡

ስለዚህ ህብረተሰባችን ለህክምና ወደ ጤና ተቋም ሲሄድ ይዞት ከሄደው በሽታ በተጨማሪ ሌላ ይዞ እንዳይመለስ፤ ወይም ይዞት የሄደውን ጥሎ ሌላ በሽታ ይዞ ወደ ቤቱ እንዳይመለስ፤ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ጤና ባለሙያዎችም የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ የአለም የጤና ድርጅት ያስቀመጠውን የእጅ አስተጣጠብ ዘዴ ተግባራዊ በማድረግ ከበሽታ አካሚና ፈዋሽ እንጅ አስተላላፊ እንዳይሆኑ በእጅጉ ጥንቃቄ ያደርጉ ዘንድ ምክራችን ነው፡፡

የዚህ ጥናት ሙሉ መረጃ ካስፈለገዎ፡ ማስፈንጠሪያዋን ይጠቀሙ፡፡
https://www.ajol.info/index.php/ejhd/article/view/178858

========================================
ተፃፈ፡ በዮሐንስ ዘነበ (ባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ ላቦራቶሪ ት/ት ክፍልና የፍልስፍና ዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ)
========================================

Methicillin-resistant Staphylococcus aureus with genotyping method among human immunodeficiency virus positive pediatric patients in Northwest Ethiopia: A cross-sectional study design | Ethiopian Journal of Health Development Methicillin-resistant Staphylococcus aureus with genotyping method among human immunodeficiency virus positive pediatric patients in Northwest Ethiopia: A cross-sectional study design Yohannes Zenebe Martha Tibebu Begna Tulu Daniel Mekonnen Zewdie Mekonnen Abstract Abstract Background: Increasing ev...

11/01/2021

የኮሮና ቫይረስ ዋና ፕሮቲየዝ ኢንዛይምና እና የመድሃኒት ኢላማነቱ
(SARS-CoV-2 main protease as a drug target)
=========================================

ሳርስ ኮሮና ቫይረስ-2 በተባለዉ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የሚመጣዉ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የጠጠረ ክንዱን በዓለም ላይ ማሳረፍ ከጀመረ እነሆ ድፍን አንድ ዓመት ሞላዉ፡፡ በብዙ መንገድ መተላለፍ መቻሉ እና ፍቱን ክትባትም ሆነ መድሃኒት ባለመገኘቱ ምክንያት ከ86 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ታመዋል፣ ወደ 1.9 ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ ህይወታቸዉን አጥተዋል፣ አለም ክፉኛ ጠላት ገጥሟት ባጅቷል፡፡ ያስከተለው ቀውስ የጤና ብቻ አይደለም፣ ዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀዉስም ጭምር እንጅ!!፡፡

የቫይረሱ ዘረ መል እንዲራባ እና ሙሉ ቫይረስ ሆኖ ሌሎች ህዋሳትን እንዲያጠቃ ከሚያደርጉ ወሳኝ የቫይረሱ አካላት መካከል ዋና ፕሮቲየዝ (main protease) የተሰኘዉ ኢንዛይም የአንበሳዉን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህ ኢንዛይም የቫይረሱ አካላት ተሰርተዉ ካለቁ በኋላ ወደ ንዑስ አካላት እንዲቆራረጡ በማድረግ በሽታ አምጪዉ ሙሉ ቫይረስ (virion) እንዲፈጠር በማድረግ በቫይረሱ የህይወት ዑደት ላይ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ማሽን ነው (ምስል 1) ፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ሳይንቲስቶች ይህን ወሳኝ ማሽን የሆነ ኢንዛይም የሚገታ መድሃኒት በማፈላለግ ላይ ሲገኙ ብዙ ተስፋ ሰጪ ዉጤቶችም በመመዝገብ ላይ ናቸዉ፡፡

ይህ ኢንዛይም የተመራማሪዎችን ትኩረት የሳበበት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ

1️⃣ ከዚህ በፊት የተከሰቱ ቫይረሶችን ማለትም ኤች አይ ቪ እና ሄፕታይትስ ሲን ለማከም የዚህን ኢንዛይም ተግባር የሚገቱ መድሃኒቶች ተሰርተዉ ዉጤታማ በመሆናቸዉ

2️⃣ ኢንዛይሙ ከሌሎች ፕሮቲኖች አንፃር ሲታይ የዘረ መል ለዉጥ የማድረግ ታሪኩ በጣም አነስተኛ ስለሆነ፡፡ ለምሳሌ የሳርስ ኮሮናቫይረስ-2 ዋና ፐሮቲየዝ ዘረ መል ከሳርስ ኮሮና ቫይረስ-1 እና መርስ ኮሮና ቫይረስ ተመሳሳይ ኢንዛይሞች ጋር ሲነፃፀር የኢንዘይሙ ገባሪ አካል (active site) መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ተመሳሳይ የዘረ መል ዉቅር (DNA sequence) አለዉ፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ በሽታዎችን መግታት የሚችሉ (broad-spectrum) መድሃኒቶችን ለመስራት ያስችላል፡፡

3️⃣ ኢንዛይሙ የተሻሻለ ክወና (enhanced catalytic activity) በማሳየቱ መድሃኒቶች በቀላሉ እንዲያጠቁት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፡፡

4️⃣ ከዚህ ኢንዛይም ጋር ተመሳሳይ ተግባር ያላቸዉ ኢንዛይሞች በሰዉ ህዋሳት ዉስጥ ስለሌሉ፤ ለዚህ ኢንዛይም መምቻ ተብለው የሚሰሩ መድሃኒቶች ከኢላማ ዉጪ (off-target) የማጥቃት እድላቸዉ ይቀንሳል፡፡ ይህም ይህን ኢንዛይም ኢላማ አድርገው የሚሰሩ መድኃኒቶች አነስተኛ መርዛማነት (low toxicity) ያላቸዉ መድኃኒቶች እንድሆኑ ያደርጋል፡፡

5️⃣ ከዚህ ባሻገር ኢንዛይሙን የሚመቱ መድሃኒቶች የሚጣበቁበት ቦታ ምቹ የሆነ መዋቅር እና ቅርፅ (structure and shape) ስላለዉ የመድሃኒቶችን ፍቱንነት ከፍ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል (ምስል 2ን ይመልከቱ)፡፡

በአሁኑ ሰዓት የኢንዛይሙን መዋቅር መሰረት ያደረጉ ብዙ የመድሃኒት ምርምሮች በኮምፒዉተር ስሌት፣ በህዋስ ምርመራ (cell culture) እና በክሊኒካዊ ሙከራ (clinical trial) ደረጀ እየተካሄዱ ሲሆን ብዙ ተስፋ የሚሰጡ ዉጤቶች እየታዩ ነዉ፡፡ ለምሳሌ 11u, 11r, 13a, 13b, N3, 11a, 11b (ምስል 3) የሚባሉ አዳዲስ መድሃኒቶች በሙከራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ለሄፕታይቲስ ሲ እና ለኤች አይ ቪ የሚሰጡ መድሃኒቶች እና ከእፅዋት የሚገኙ ባህላዊ ቅመሞች የዚህን ኢንዛይም ተግባር በማስተጓጎል ደረጃ የተሻሉ መሆናቸው ምናልባትም በቅርብ ቀን በሽታዉን የሚገታ መድሃኒት ሊኖር እንደሚችል አመላካች ነዉ፡፡

ይሁን እንጅ በሙከራ ላይ የሚገኙ ብዙ መድሃኒቶች ያሉበት የመድሃኒት ቅመማ ደረጃ ገና እንጭጭ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሰዉ ህዋሳት ዉስጥ ምን ያህል ዉጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ የታወቀ ነገር የለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሌሎች የቫይረሱ ክፍሎች ላይ የሚደረጉ የዘረ መል ለዉጦች የዚህን ኢንዛይም መዋቅር ይብዛም ይነስም መለወጥ መቻላቸዉ ተረጋግጧል፡፡ ስለሆነም እጩ መድሃኒቶች ሲዘጋጁና ምርምሮች ሲካሄዱ ይህን ጉዳይ ታሳቢ ያደረጉ መሆን አለባቸው፡፡ይህን መሰል ምርምሮች ሲደረጉ የተላያዩ የሙያ ዘርፎች ቢካተቱ ጠቀሜታው የላቀ ስለሚሆን ታሳቢ እንዲደረግ አንመክራለን፡፡

--------------------------------------------------------------------------
ተፃፈ፡ በኃይለማርያም ምህረቴ (ከደብረ ማርቆስ የኒቨረሲቲ፣ በቻይና የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የባዮኬሚስትሪና ሞለኪዩላር ባዮሎጂ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ)
--------------------------------------------------------------------------

ለበለጠ መረጃ
1. Zhang, L., Lin, D., Sun, X., Curth, U., Drosten, C., Sauerhering, L., . . . Hilgenfeld, R. (2020). Crystal structure of SARS-CoV-2 main protease provides a basis for design of improved α-ketoamide inhibitors. Science, 368(6489), 409-412.
2. Mengist, H. M., Fan, X., & Jin, T. (2020). Designing of improved drugs for COVID-19: Crystal structure of SARS-CoV-2 main protease M pro. Signal Transduction and Targeted Therapy, 5(1), 1-2.
3. Dai, W., Zhang, B., Jiang, X.-M., Su, H., Li, J., Zhao, Y., . . . Liu, F. (2020). Structure-based design of antiviral drug candidates targeting the SARS-CoV-2 main protease. Science, 368(6497), 1331-1335.
4. Ullrich S, Nitsche C. The SARS-CoV-2 main protease as drug target. Bioorg Med Chem Lett. 2020 Sep 1;30(17):127377. doi: 10.1016/j.bmcl.2020.127377. Epub 2020 Jul 2. PMID: 32738988; PMCID: PMC7331567

11/01/2021

ማይክሮፕላስቲክ
========
ማይክሮፕላቲኮች በትንሹ ተቆራርጠው እና ተበታትነው የሚገኙ ፕላስቲኮች ማለት ነው፡፡ ከትንሽነታቸውም የተነሳ በአየር ላይ ሊንሳፈፉ እና ወደ ሰው መተንፈሻ አካል ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከዛም አልፈው በሳንባ እና በአንጀት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ መጠናቸውን በልኬት ለማስቀመጥ ያህል ከ5 ሚሊሜትር ያነሱ እና በዓይን እስከማይታዩ ድረስ ትንሽ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ማይክሮፕላስቲኮች በኢንደስትሪዎች ውስጥ ለተለያየ ጥቅም ሲባል ሊፈበረኩ ይችላሉ፡፡

በተጨማሪም ከተሰባበረ እና ከተቆራረጠ ፕላስቲክ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
በተደረጉ ሳይንሳዊ ጥናቶች፣ ማይክሮፕላስቲኮች የሰው ልጅ ዓይነምድር ውስጥ እየተገኙ እንደሆነ ተጨባጭ ማስረጃዎች እየቀረቡ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው በሰው ልጅ አፍ በኩል ገብተው፣ በአንጀት ውስጥ አልፈው እንደሚወጡ ነው፡፡ ስለዚህ ከምግብ ማንሸራሸሪያ አካላት ወይም ከአንጀት እና ሆድ ዕቃ ጋር ተያያዥ የጤና ዕክል ላለባቸው ሰዎች የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ባለፈ የሚያመጣው የጤና ዕክል መጠን ስለማይታወቅ፤ ለቀጣይ ጊዜያት ምን ያህል ጉዳት ማድረስ እንደሚችል እና መፍትሄው ላይ ብዙ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሌላኛው የማይክሮፕላስቲኮች በጨው ውስጥ መገኘት ነው፡፡ ምክንያቱም ጨው የሚገኘው ከባህር እና ከውሃ አካላት እንደመሆኑ እና የውሃ አካላትም በፕላስቲክ ቆሻሻዎች እየተበከሉ ያሉ በመኖራቸው ነው፡፡

ስለዚህ በጤና ላይ የሚያደርሱትን ዕክሎች በጥናት ታውቆ እስኪረጋገጥ ድረስ መፍትሔው ላይ ማተኮር ወሳኝ እና አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ በቤታችን፣ በዙሪያችን እና በአካባቢያችን የሚገኝ ማንኛውንም ዓይነት ፕላስቲኮች ሳይቆራረጡ እና ሳይሰባበሩ በተገቢው ሁኔታ ማስወገድ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

ተፃፈ፡
በ Alula (Anley) Teferra (Ph.D. candidate)
Microbiology (Cell), Pukyong National University, Korea
(27/04/2013 ዓ.ም)

Want your practice to be the top-listed Clinic in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Category

Website

Address

Addis Ababa