Shalom Medical Consultancy

Shalom Medical Consultancy

Share

08/07/2022

"የተሰራልኝ ኦፕሬሽን ምን እንደነበር እና ለምን እንደ ተሰራልኝ አላውቀውም!"

ከተለመዱት የአዳር የስራ ፕሮግራሜ በአንዱ ነው... አንድ በ40 ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ ያለ ጎልማሳ በጠና ታሞ ወደ ቀዶ ህክምና ድንገተኛ ህክምና ክፍል መምጣቱ ተነግሮን እሱን ለማየት ሄድን።
ገና ሲታይ በጽኑ ህመም መታመሙ ያስታውቃል። ያቃስታል...ሆዱ በጣም ከመቆዘሩ የተነሳ የደረሰች ነፍሰ ጡር አስመስሎታል። ቀርበን ካየነው በኋላ መደ መመርመርያ ክፍል አስገብተን ጫጫታ በሌለበት ሁኔታ ስለ ህመሙ ሁኔታ መጠየቅ ጀመርን። ህመሙ ሦሥት ቀን እንደሆነው ...በእነዚህ ቀናትም... እያደር የሆዱ መቆዘር እና ቁርጠት እየጨመረ መምጣቱን በተያያዘም እንደሚያስመልሰው እና ሰገራም ሆነ ፈስ እንዳልወጣው ነገረን። ሌሎች አስፈላጊ ምልክቶች እንዳሉት እና እንደሌሉት ከጠየቅን በኋላ.... ሰውነቱን ለመመርመር ልብሱን እንዲገልጥ ጠይቀን ምርመራው ተጀመረ። ሆዱ ላይ ቁልቁል በእንብርቱ የሚያልፍ የቆየ የኦፕሬሽን የሚመስል ጠባሳ አለ። የበፊቱ ኦፕሬሽን በሌላ ሀስፒታል የተሰራ በመሆኑ አሁን ስለያዘው በሽታ ምንነት ለማወቅ ፍንጭ ስለሚሰጠን እንደገና መጠየቅ ጀመርን።
"ይሄ መቼ የተሰራ ኦፕሬሽን ነው?"
" የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ ነው" አለ እያቃሰተ።
" በምን ምክንያት ነበር የተሠራው ኦፕሬሽኑ?" ቀጣዩ እና አስፈላጊው ጥያቄ ተጠየቀ።
"እሱን አላውቀውም.... ብቻ ያኔም እንዳሁኑ ሆዴን በጣም ታምሜ ነው በድንገተኛ የተሰራልኝ" አለ የምርመራ አልጋው ላይ እየተገላበጠ።
" ስለ ህመሙ ምንነት ተነግሮህ ነበር?....ከኦፕሬሽኑ በኋላስ ለምርመራ የተላከ ናሙና ነበር? ...... የዛን ጊዜም ካሁኑ ህመምህ ጋር ተመሳሳይ ምልክቶች ናቸው የነበሩት?...ወዘተ "
ስለ በፊቱ ኦፕሬሽን ብዙ ጥያቄዎችን አከታትለን ብንጠይቅም...ከታማሚውም ሆነ ከአስታማሚዎቹ በቂ መረጃ ማግኘት አልቻልንም ነበር። አሁን ስላለው ህመሙ ለማወቅ ትልቁን እና ዋናውን መረጃ ማግኘት ሳንችል ቀረን። የአካል ምርመራውን ከጨረስን በኋላ አስፈላጊ የራጅ እና የላብራቶሪ ምርመራዎችን ልከን ኦፕሬሽን የሚያስፈልገው ህመም ነበር እና በዚህም ከተስማማን በኋላ ይዘነው ወደ ኦፕሬሽን ገባን።

ለመሆኑ ....
1. አንድ ታካሚ ኦፕሬሽን ሊሰራለት ሲወሰን ስለ በሽታው ምንነት የመጠየቅ መብት አለው?
2. ኦፕሬሽን ለምን እነደሚሰራለት እንዲሁም ኦፕሬሽን ባይሰራ ሌላ የህክምና አማራጭ እንዳለው የመጠየቅስ መብት አለው?
3. ኦፕሬሽኑን ተከትሎ ሊመጡ ስለሚችሉ ተያያዥ ችግሮችስ ማብራርያ ሊደረግ ይገባል?
4. ኦፕሬሽኑን የሚሰራው ባለሞያስ ስለ በሽታው እና ስላሉት የህክምና አማራጮች እንዲሁም ተያይዘው ስለሚመጡ ችግሮች ለታካሚው እና ቤተሰቡ ማብራርያ የመሰጠት ግዴታ አለበት?

እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች የሚመልስልን ማንኛውም ኦፕሬሽን (መለስተኛም ሆነ ከባድ) ከመሰራቱ በፊት በኦፕሬሽን ባለሞያው እና በታካሚው( ቤተሰቡ) መኃል የሚደረገው የስምምነት ቅጽ(Consent form) ነው።
ይህ የስምምነት ቅጽ በተለያዩ ሆስፒታሎች መጠነኛ የይዘት ልዩነት ቢኖረውም ከሞላ ጎደል ወሳኝ በሆኑ ነጥቦች ላይ ሁሉም ተመሳሳይ ይዘት አላቸው።
የቅድመ ኦፕሬሽን የስምምነት ቅጽ ታካሚው እና ቤተሰቡ በቅጹ ላይ ከመፈረማቸው በፊት መሞላት ያለበቸውን አስፈላጊ ጥያቄዎችን ይይዛል። ከእነዚህም መኃል የሚከተሉት ይገኙበታል።
፨ ኦፕሬሽኑ የሚሰራለት ታካሚ ስም....
፨ ኦፕሬሽኑን የሚሰራው ባለሞያ/ዎች ስም....
፨ ታካሚው(ቤተሠቡ) ስለ በሽታው ምንነት ያውቃሉ ወይስ አያውቁም ......
፨ በሽታው ምንድን ነው....
፨ ኦፕሬሽኑ የሚሰራው በምን ምክንያት ነው? .....
፨ በኦፕሬሽኑ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች ምንድን ናቸው?...
፨ ከኦፕሬሽን ውጪ ሌላ የህክምና አማራጭ አለው ወይ? ....
፨ ኦፕሬሽን ባይሰራ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮች ምን ምን ናቸው?....
፨ በኦፕሬሽኑ ሰዓት ታካሚው ደም ቢያስፈልገው ለመውሰድ ፈቃደኛ ነው ወይ?...... እና ወዘተ

ማንኛውም ታካሚ ድንገተኛም ሆነ ድንገተኛ ላልሆነ ህመም፤ መለስተኛም ሆነ ከባድ ኦፕሬሽን ከማሰራቱ በፊት ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች ኦፕሬሽኑን ከሚሰራው ባለሞያ ጠይቆ የመረዳት መብት አለው። ባለሞያውም ስምምነቱን ከማስፈረሙ አሥቀድሞ እነዚህን እና ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን ለታካሚው እና ቤተሰቡ የማስረዳት ግዴታ አለበት። ይህን ማድረጉ አሁን አሁን እየታየ ያለውን በታካሚ እና በባለሞያው መኃል ያለ አለመተማመን.... እና አስፈላጊም ሆነ አላስፈላጊ መወነጃጀል ሊቀንስ ይችላል። በተለምዶም ከህክምናው በኋላ የሚከሰቱ ችግሮችን ታካሚው እና ቤተሰቡ... እንዲሁም ዩቲዩበሮች... "የህክምና ስህተት ነው" እያሉ ጣታቸውን ወደ ባለሞያው እንዳይቀስሩ የራሱ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። በማንኛውም መለስተኛም ሆነ ከባድ ኦፕሬሽን ወቅት የታካሚውን እና ቤተሰቡን መልካም ፈቃድ ያማከለ ኦፕሬሽን መሰራት እንዳለበትም ግንዛቤን ይፈጥራል።

Photos from Shalom Medical Consultancy's post 12/05/2022

የማንኮራፋት ችግር | Snoring disorder

"የማንኮራፋት ችግር ማህበራዊ ጫና ከመፍጠሩ ባሻገር ጤና ላይ የሚያመጣዉ መዘዝ የጎላ ነው።

የማንኮራፋት ችግር የሚከሠተዉ አየር ከሳንባ ወይም ወደ ሳንባ በሚወጣበት እና በሚገባበት ጊዜ በሚያልፍባቸው የአየር ቱቦ በቂ የሆነ ክፍተት ካላገኘ ወይም የሚያልፍበትን የተመቻቸ መስመር የሚያስቀይር ችግር ካጋጠመው የሚፈጥረው የተዛባ ድምጽ (turbulent air flow) ነው።

ይህን የማንኮራፋት ችግር የሚያስከትሉ ምክነያቶች በህጻናት እና አዋቂዎች ላይ የተለያዩ ቢሆንም የሚከሠቱበትን ቦታ በ 4 ከፍሎ ማየት ይቻላል።

1. ከአፍንጫ እስከ ላንቃ ያለው የአየር መተላለፊያ ሲሆን ህጻናት ላይ በአብዛኛው አዴኖይድ የምንለው የቶንሲል ክፍል መጠን መጨመርና በአፍንጫ የሚያልፈውን አየር ሲዘጋ የሚከሠት ነው። አዋቂወች ላይ ከዚህ ቦታ በሚነሳ ችግር ማንኮራፋት ከተከሠተ ካንሠርን ጨምሮ ሌሎች እብጠቶችን ማሠብ እና ምርመራ ማድረግ ግድ ይላል።

2. ከምላስ የኋለኛው ክፍል እና በጎኑ ከሚገኙ ቶንሲሎች (posterior tounge and palataine tonsilar hypertrophy) ጋር ተያይዞ የሚከሠት ማንኮራፍት ነው። የዚህ ከምላስ ጎን የሚገኘው ቶንሲል የማንኮራፍት ችግር ከመፍጠሩ በላይ በ ተደጋጋሚ የቫይረስ እና የባክቴሪያ ኢንፌክሽን በመፍጠር ተጨማር የጤና እክል ያስከትላል።

3. በአፍና መንገጭላ አካባቢ የሚከሠቱ የአፈጣጠር ችግሮች እንዲሁም ከነዚህ ቦታወች ተነስተው የኅለኛውን የአየር መተላላፊያ ሊዘጉ የሚችሉ እብጠቶች እንደ ምከንያት ይጠቀሳሉ።

4. የኋለኛው የአየርና የምግብ የጋራ መተላለፊያ ግድግዳን የሚሠሩ ጡንቻወች መዛል ፣ በስብ መሞላት ፣ በእብጠት መጠቃት ወይም መግል መቋጠር ከተፈጠረ የሚከሠት ይሆናል።

ማንኮራፍት የሚከሠትባቸውን ምክነያቶች በወፍ ዘረር ካየን የዚህ ችግር መጠን ከሠው ሠው እንደተፈጠረው የአየር መተላለፊያ መስመር መጥበብ መጠን ይለያያል። ይሔም ከልማዳዊ ማንኮራፍት (habitual snorer) እስከ ሳንባ ከረጢቶች መጠን መቀነስ (pulmonary alveolar hypoplasia) ብሎም የሳንባ ደም ስሮች ግፊት እና የልብ ችግር ሊፈጥር ይችላል።

በተጨማሪም አካላዊና አእምሯዊ የእድገት ችግር ፣ የጸባይ ችግር (በተለይም ህጻናት ላይ) ፣ ቀን አብዝቶ የመተኛት ችግር ፣ በስራ የመዛልና ውጤታማ ያለመሆን እና የመሳሠሉ ተጽኖወችን ይፈጥራል።

በትዳር አጋር ላይ የሚፈጥረው ጫና እና ማህበራዊ ቀውሡም ሌላው ጉዳቱ ነው። ማንኮራፍት የፈጠረውን የጤና ችግር ደረጃ ለማወቅ አይነተኛ የሚባለው መሣሪያ (polysomnography ) ሲሆን በሀገራችን የለም ማለት ይቀላል። ነገር ግን ይሔንን ለመተካት የሚፈጠሩ ስሜቶችን እና ምልክቶችን በማየት እና የልብ ፣ የአተነፋፈስ ምርመራወችን በማድረግ ደረጃውን ማወቅ ይቻላል። የዚህን ጀረጃ ማወቁ ጥቅሙ ለእያንዳንዱ ደረጃ የሚሠጠው ህክምና የተለያየ መሆኑ ነዉ።

ወደ መፍትሔው ስንመጣ ፤ መፍትሔው የሚወሠነው ማንኮራፍቱን በፈጠረው ችግር እና የችግሩ መጠን ሲሆን

1. በአብዛኞች ህጻናት ላይ ከአፍንጫ ጀርባ እና ከምላስ ጎን ያለውን ቶንሲል በሠርጀሪ በማስወገድ የሚስተካከል ይሆናል።

2. በአዋቂወች ደግሞ እባጮች (እጢወች) እንደሌሉ ከተረጋገጠ በኋላ ክብደት መቀነስ ፣ የኦክስጅን ህክምና (CPAP) ብሎም የአየር መተላለፊያን ቱቦ ለማሥፍት የ ሚደረጉ ሠርጀሪወች (uvuloplalatopharyngoplasty
,uppp እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ሠርጀሪወች) የህክምና አማራጮች ናቸው።

ስለዚህ፦ ማንኮራፋትን እንደ ቀላል ችግር በማየት አንዘናጋ፤ቢያንስ ያለንበት የማንኮራፍት ጀረጃ በምን መሥተካከል እንደሚችል ሀኪሞችን እናማክር።"

ዶ/ር አለማየሁ እሸት (ከአንገት በላይ ስፔሻሊስት ፣ መምህር እና ረዳት ኘሮፌሰር )
Via

Photos from Shalom Medical Consultancy's post 11/05/2022

"ህፃናት መች ነው ጥርስ ማብቀል ያለባቸው?"

"ህፃናት እስከ መች መብቀል አለበት? ካልበቀለ መች ወደ ባለሙያ መመሄድ አለባቸው? የጥርስ መብቀል ከተቅማጥ በሽታ ጋር ይገናኝ ይሆን? ስለ ህፃናት የጥርስ እድገት ትንሽ ጀባ ልበላችሁ

ብዙ እናቶች ልጆቻቸው ጥርስ መች ማብቀል እንደሚጀምሩ በግልፅ ስለማያውቁ ልጄ እስካሁን ጥርስ አላበቀለም/ አላበቀለችም ብለው ጤና ተቋም ሲመጡ ማየት የተለመደ ነገር ነው። አንዳንድ እናቶች ደግሞ እስከመች ድረስ ሊያድግ እንደሚችል አያውቁም በዚህ የተነሳ እራሳቸውን ሲያጨናንቁ እናያለን ይህን ጭንቀታቸውን ለመቅረፍ እኔም ካነበብኩት ትንሽ ጀባ አልኳችሁ።

የህፃናት የጥርስ እድገት በጨቅላዎች እና በልጆችዎ ድድ ውስጥ የጥርስ መብቀልን ያመለክታል ይህ የሚጀምረው ብዙውን ጊዜ ልጅዎ ከ6 እስከ 8 ወር ዕድሜ ሲኖረው ሲሆን፡፡ ልጅዎ የ30 ወራት ዕድሜ ላይ ሲደርስ ሁሉም 20 የህጻናት ጥርሶች ቦታቸውን ይይዛሉ ፡፡

አንዳንድ ልጆች ግን ከ8 ወር ዕድሜያቸው በሗላም ቢሆንም ምንም አይነት ጥርስ ላያሳዩ ይችላሉ ፣ ይህ ግን ብዙውን ጊዜ የተለመደ ቢሆንም ምንም ጥርስ አስከ 13 ወር ካልበቀለ ለባለሙያ ማሳየት ይገባል፡፡

ብዙውን ጊዜ ሁለቱ የታችኛው የፊት ጥርሶች (የታችኛው ኢንሲዘሮች) ቀድመው ይበቅላሉ፡፡ ቀጥለው ሁለቱ የላይኛው የፊት ጥርሶች (የላይኛው ኢንሲዘሮች) ያድጋሉ፡፡

ከዚያም ሌሎች ወተት ጥርሶች (ኢንሲዘሮች) ፣ የላይኛውና የታችኛው መንጋጋዎች ፣ የውሻ ክራንቻዎች፣ በመጨረሻም የላይኛውና የታችኛው በጥልቀት የሚገኙት መንጋጋዎች ይበቅላሉ፡፡

ልከጆች ጥርስ ማብቀል ሲጀምሩ ምን አይነት ምልክቶች ያሳያሉ ??

- መነጫነጭ ወይም ብስጩነት ማሳየት
- ጠንካራ ነገሮችን መንከስ ወይም ማኘክ
- ልጋግ ማዝረብረብ ብዙውን ጊዜ ጥርስ ማደግ ከመጀመሩ በፊት የሚከሰት ነው
- የድድ ማበጥና መጠንከር
- ምግብ እምቢ ማለት
- የእንቅልፍ ለመተኛት መቸገር

መፍትሄውስ ምን ይሆን?

በዚህ ጊዜ ማድረግ ያለብን ልጅዎ የማያኝካቸው ቀዝቃዛ ነገሮች መስጠት። ለልጅዎ ለስለስ ያሉ ምግብ ይስጦቸው ፤ በቀስታ ጥርስ የሚበቅልበት ቦታ በእጅ መንካት። በዚህ መንገድ የልጅዎን የጥርስ እድገት አብረው በመሆን የተሳካ ያድርጉላቸው።"

"መልካሙን ሁሉ ተመኘው"
ዶ/ር መሐመድ በሽር (የህፃናት ሐኪም)
Via Hakim

Want your business to be the top-listed Health & Beauty Business in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Category

Website

Address

Swazeeland Street
Addis Ababa
1271